ነሐሴ 25 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ)በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የተከሰተው እና አሁንም ድረስ የብዙዎችን ሕይወት እየቀጠፈ የሚገኘውን የኢቦላ ወረርሽኝ ለመከላከል፣ አስቀድሞ የባለሙያዎች የተግባር ልምምድ እያካሄደ መሆኑን የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ለመናኸሪያ ሬዲዮ አስታውቋል፡፡ የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ኃይሉ፣ ወረርሽኙን ለመከላከል ከጎረቤት ሀገራት ጋር በመተባበር መረጃ የመለዋወጥና ባለሙያዎችን ዝግጁ የማድረግ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል፡፡ ወረርሽኙ ከተከሰተባቸው አካባቢዎች በርካታ ዜጎች ለተለያዩ ጉዳዮች ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጡ የገለጹት ዶክተር መሳይ፣ ይህም ሁኔታ የተጋላጭነት መጠንን ከፍ እንደሚያደርገው አስረድተዋል፡፡ ኢንስቲትዩቱ በሽታው በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ በአየር መንገድና በድንበር አካባቢዎች ከፍተኛ የቅኝት ሥራ እያካሄደ መሆኑንም ገልጸዋል። ወረርሽኙ በኢትዮጵያ ባይከሰትም፣ በተከሰተበት አካባቢ በሰዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ በመሆኑ የላቦራቶሪ እና ሌሎችም የዝግጁነት ሥራዎች ካለፉት ጊዜያት ተጠናክረው መቀጠላቸውን አስታውቀዋል፡፡ በድንበር አካባቢዎች፣ በክልሎች እንዲሁም በአየር መንገድ ወረርሽኙ ቢታይ አፋጣኝ ምላሽ መስጠት የሚችሉ ባለሙያዎች የተግባር ልምምድ እንዲያደርጉ ሥራዎች መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡ በዚህም ለበርካታ ባለሙያዎች አስቀድሞ ስልጠና መሰጠቱን ያመላከቱት ዋና ዳይሬክተሩ፣ በተለይ በድንበር አካባቢ ያሉ ባለሙያዎች በቂ የቅኝት ሥራ የሚሰሩባቸው ግብዓቶች ዝግጁ መደረጋቸውን ጠቁመዋል፡፡ በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በኢቦላ ወረርሽኝ ከ5 ሺህ በላይ ዜጎች ተጠቂ መሆናቸውን የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ያመላክታል፡፡
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ