ነሐሴ 22 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ) የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘሌንስኪ የስፔስ ኤክስ (SpaceX) ባለቤት ለሆኑት ኢሎን መስክ የሀገሪቱን ከፍተኛ የክብር ሜዳሊያ የሆነውን «የነጻነት ኦርደር» (Order of Freedom) መስጠታቸውን ይፋ አደረጉ። ይህ ሽልማት የተበረከተው የስታርሊንክ (Starlink) የሳተላይት ኢንተርኔት አገልግሎት በሀገሪቱ የጦርነት ወቅት ለሰው ልጅ ህይወት ጥበቃ፣ ለነጻነት እና በአሜሪካና ዩክሬን ህዝቦች መካከል ያለውን ግንኙነት በማጠናከር ላበረከተው ከፍተኛ አስተዋጽኦ እውቅና ለመስጠት መሆኑ ተገልጻል። ሩሲያ እና ዩክሬን እ.ኤ.አ. በ2022 ሙሉ በሙሉ ወደ ጦርነት ከገቡበት ጊዜ ጀምሮ መስክ የስታርሊንክ አገልግሎትን ለዩክሬን ክፍት ያደረገ ሲሆን፣ ይህም የሀገሪቱ ጦር በግንባር ላይ ለሚያደርገው የመገናኛ ዘዴ እና ለድሮን ኦፕሬሽኖች ዋና የህይወት መስመር ሆኖ አገልግሏል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህም ስፔስ ኤክስ የሩሲያ ኃይሎች በህገ-ወጥ መንገድ ይጠቀሙባቸው የነበሩ በሺዎች የሚቆጠሩ የስታርሊንክ መሳሪያዎችን አገልግሎት ማቋረጡ የዩክሬንን የደህንነት የበላይነት አጠናክሯል። ይህ ከፍተኛ እውቅና የተሰጠው ኪየቭ የስታርሊንክ አገልግሎት በሩሲያ ግዛት ውስጥ በሚገኙ የጦር ካምፖች ላይ ለሚደረጉ የድሮን ጥቃቶች እንዲውል ፍቃድ ለማግኘት ጥረት በማድረግ ላይ ባለችበት ወቅት ነው። ኢሎን መስክ አገልግሎቱ በሩሲያ ግዛት ላይ እንዲስፋፋ መፍቀድ የጦርነቱን ሁኔታ ያባብሳል በሚል ስጋት መጀመሪያ ላይ ቢቃወመውም፣ ዩክሬን አሁንም ድርድሩን በመቀጠል አዎንታዊ ምላሽ ለማግኘት ጥረት እያደረገች ትገኛለች።
__ ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ