ነሐሴ 08 ቀን 2018 (መናኸሪያ ሬዲዮ) በመዲናዋ ድጋፍ እና እንክብካቤ የሚያስፈልጋቸው ሕፃናት ቁጥር እየጨመረ እንደሆነ በተደጋጋሚ ይገለፃል። እነዚህን ሕፃናት ለመርዳት በመዲናዋ ከሚገኙ ተቋማት ሠራተኞች ደመወዝ 1 በመቶ እየተቆረጠ ድጋፍ እየተደረገላቸው እንደሆነ፣ የአዲስ አበባ ሴቶች፣ ሕፃናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ የሕፃናት መብትና ደኅንነት ማስጠበቅ ዳይሬክተር አቶ አንዱዓለም ታፈሰ ለጣቢያችን ገልፀዋል።
በተለይም ወላጆቻቸውን ያጡ፣ አሳዳጊ የሌላቸው እና በጎዳና ላይ የሚገኙ ሕፃናት እንዲማሩ፣ የመኖሪያ ስፍራ እንዲያገኙና ሌሎች መሠረታዊ ነገሮች እንዲሟሉላቸው በማድረግ ረገድ የነዚህ ተቋማት ድጋፍ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ይህንን ድጋፍ ተቋማቱ በቀጥታ በገንዘብም ሆነ በአይነት ራሳቸው የሚያደርጉ ሲሆን፣ ቢሮው እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ለይቶ የማገናኘት ሥራ ብቻ እንደሚያከናውን ገልፀዋል።
በ2018 በጀት ዓመት በዚህ ድጋፍ ተጠቃሚ የሆኑት ሕፃናት ቁጥር 5 ሺህ 8 መቶ 89 እንደነበርና በ2019 በጀት ዓመት ቁጥሩን ወደ 6 ሺህ 7 መቶ ከፍ በማድረግ በችግር ውስጥ የሚገኙ ሕፃናት እንዲደገፉ እየተሠራ መሆኑን አቶ አንዱዓለም አንስተዋል።
ይህ የ1 በመቶ ድጋፍ በተቋማት በኩል እየጨመረ ቢመጣም፣ አሁንም ብዙ ቀሪ ሥራዎችና ግንዛቤ እንደሚያስፈልግ የቢሮው የሕፃናት መብትና ደኅንነት ማስጠበቅ ዳይሬክተር አቶ አንዱዓለም ታፈሰ ተናግረዋል። በዚህ የድጋፍ ፕሮግራም ውስጥ የመንግሥት ተቋማት ብቻ ሳይሆኑ የግል ድርጅቶችና ባለሀብቶች ተሳታፊነታቸው ቢጨምር በርካታ ሕፃናትን መደገፍ እንደሚቻል ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።
ተቋማት የ1 በመቶ ድጋፍ በማድረግ ለችግር የተጋለጡ ሕፃናትን በመደገፍ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተመላክቷል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ