ሰኔ 12 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ) ሊቨርፑል ከተጫዋቹ ወኪሎች ጋር ይፋዊ ንግግር ከጀመረ ሰነባብቷል፤ ይሁን እንጂ ያቀረበው 100 ሚሊዮን ዩሮ ክለቡ አርቢ ላይፕዚግ ተጫዋቹን ከሚገምተው 120 ሚሊዮን ዩሮ ያነሰ በመሆኑ ውድቅ ሊሆን ችሏል።
ሞሀመድ ሳላህን መተካት ከባድ ቢሆንም፣ አንጋፋው ግብፃዊ ኮከብ ክለቡን መልቀቅ እንደሚፈልግ ማሳወቁን ተከትሎ ሊቨርፑል ተተኪ የመፈለጉን ትልቅ የቤት ስራ በተጠናከረ መልኩ መጀመሩን ለክለቡ ቅርብ የሆነው ‘Anfield Index’ የተሰኘው የመረጃ ምንጭ ዘግቧል።
የላይፕዚጉ ኮከብ ቁጥር ስፍር በሌላቸው ታላላቅ ክለቦች በጥብቅ የሚፈለግ የግራ ክንፍ አጥቂ ነው። ተጫዋቹ ከክለቡ ባለፈ በአሁኑ ወቅት እየተካሄደ ባለው የዓለም ዋንጫ (እንዲሁም ባለፈው የአፍሪካ ዋንጫ) ላይ ለሀገሩ ኮትዲቫር እጅግ ወሳኝ እንቅስቃሴ በማድረግ ድንቅ ብቃቱን እያሳየ ይገኛል።
የቡንደስሊጋ ኮከቦችን ወደ እራሱ በማስኮብለል የሚታወቀው ባየር ሙኒክን ጨምሮ ሪያል ማድሪድ፣ አርሰናል እና ማንቸስተር ሲቲ የተጫዋቹን ሁኔታ በቅርብ እየተከታተሉ ይገኛሉ። ይህንን የ19 ዓመት ወጣት አይቮሪያዊ ተጫዋች በእጃቸው ለማስገባት ጥረት እያደረጉ ባሉበት በዚህ ሰዓት፣ የተጫዋቹ አባት የሊቨርፑል ደጋፊ መሆናቸውን መናገራቸው ግን ሊቨርፑል ተጫዋቹን ለማስፈረም ከሌሎች ቡድኖች የተሻለ ዕድል እንዳለው ፍንጭ የሰጠ ጉዳይ ሆኗል።
ኳስ ሲይዙ የሚያስፈሩ የክንፍ አጥቂዎች በጠፉበት በዚህ ዘመን፣ ያን ዲዮማንዴ እጅግ አስገራሚ ተሰጥኦ፣ አቅም እና የግል ክህሎት ያለው ተጫዋች መሆኑን እያረጋገጠ ነው።
ይህ የ19 ዓመት ወጣት የአውሮፓ እግር ኳስ ህይወቱን “ሀ” ብሎ የጀመረው በስፔኑ ሌጋኔስ ክለብ ሲሆን፣ በቆይታውም 2 ጎሎችን አስቆጥሮ 6 ኳሶችን አመቻችቶ ማቀበል ችሏል።
በሂደት ግን የበርካታ ክለቦችን ትኩረት መሳብ የቻለ ድንቅ እንቅስቃሴ በማሳየቱ ወደ አርቢ ላይፕዚግ ሊዛወር ችሏል።
ሊቨርፑል የሬድ ቡል ላይፕዚጉን ኮከብ ለማስፈረም በሚያደርገው ጥረት ውስጥ ትልቅ መነቃቃት ተፈጥሯል።
አዲሱ አሰልጣኝ አርኔ ስሎት በክረምቱ የዝውውር መስኮት ተጫዋቹን ወደ አንፊልድ ለማምጣት ከፍተኛ ፍላጎት ያላቸው ሲሆን፣ ላይፕዚግም ለተጫዋቹ የሚገባውን የገንዘብ ዋጋ ካገኘ ለመልቀቅ ፈቃደኛ መሆኑ ተሰምቷል።
የያን ዲዮማንዴን የእግር ኳስ ጉዞ በቁጥሮች ስንመለከት፣ በክለብ ደረጃ እስካሁን ባደረጋቸው 29 ጨዋታዎች 12 ግቦችን ከመረብ አሳርፎ 8 አመቻችቶ ማቀበሎችን (አሲስት) አስመዝግቧል።
በዚህ በ2025/26 የውድድር ዘመን በቡንደስሊጋው ባሳየው አስገራሚ ብቃት ከ2,000 ደቂቃዎች በላይ ሜዳ ላይ መቆየት የቻለ ሲሆን፣ 89 በመቶ የተሳካ የኳስ ቅብብል ስኬት አለው። በተለይም ተከላካዮችን በአንድ ለአንድ ግንኙነት አታሎ የማለፍ (Dribbling) ብቃቱ፣ ፍጥነቱ እና ኳስን ከመከላከል መስመር መስርቶ የመውጣት ችሎታው ለሊቨርፑል የአጨዋወት ዘይቤ ተመራጭ ያደርገዋል።
ሊቨርፑል ዲዮማንዴን ለማስፈረም 100 ሚሊዮን ዩሮ ለማቅረብ ዝግጁ መሆናቸውን ‘The Athletic’ ቢዘግብም፣ ከዚህ በላይ ሊጠየቁ እንደሚችሉ ይገመታል። የባየር ሙኒክ ፍላጎት መቀዝቀዝ ዝውውሩን ቀላል ያደርገዋል ተብሎ ቢታመንም፣ የፈረንሳዩ ሀያል ቡድን ፓሪስ ሴንት ጄርሜንም (PSG) ተጫዋቹን የመፈለግ ፍላጎት አለው። ይሁን እንጂ ፒኤስጂ እስካሁን ይፋዊ የዝውውር ጥያቄ አላቀረበም፤ ላይፕዚጎችም ተጫዋቹ ራሱ ወደ የትኛው ክለብ ማምራት እንደሚፈልግ ውሳኔውን እንዲያሳውቃቸው መክረውታል።
ያን ዲዮማንዴ በብዙ ውጣ ውረድ እዚህ የደረሰ ተጫዋች ሲሆን፣ ዘንድሮ በቡንደስሊጋው በርካታ የተሳኩ ድሪብሎችን በማድረግ ስሙ ከፊት የሚቀመጥ ተጫዋች ነው። በአማካኝ በ90 ደቂቃ ውስጥ 4.3 የተሳኩ ድሪብሎችን በማድረግ ቀዳሚው ነው።
በዓለም ዋንጫው ላይ እንኳን ሀገሩ ኮትዲቫር ኤኳዶርን 1 ለ 0 ስታሸንፍ፣ ከሞከራቸው 6 ድሪብሎች ውስጥ 4ቱ የተሳኩ ነበሩ፤ ይህም የጨዋታው ኮከብ (Man of the Match) ተብሎ እንዲመረጥ አድርጎታል።
የSky Germanyው ጋዜጠኛ ፍሎሪያን ፕሌተንበርግ በX (ቲዊተር) አካውንቱ ባጋራው መረጃ መሠረት፣ ሊቨርፑል ተጫዋቹን የሳላህ ቀጥተኛ ተተኪ አድርጎ እየተመለከተው በመሆኑ ይህ ዝውውር የመከናወን ዕድሉ ሰፊ ነው።
ሊቨርፑል ያን ዲዮማንዴን ለማስፈረም የሚፈልገው በአጥቂ መስመሩ ላይ ተጨማሪ ፍጥነት እና የፈጠራ አቅም ለመጨመር ሲሆን፣ ተጫዋቹ በሁለቱም የክንፍ መስመሮች ላይ እኩል የመጫወት ብቃት አለው።
አሰልጣኙ ለቡድናቸው የክንፍ ማጥቃት እንቅስቃሴ ይህ ተጫዋች ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት ያምናሉ። ከዓለም ዋንጫው መጠናቀቅ በኋላ ተጫዋቹ ወዴት ያመራል የሚለው ርዕሰ ጉዳይ በዓለም እግር ኳስ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት ይጠበቃል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ