ሰኔ 11 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ) በ2018 በጀት ዓመት 11 ወራት ውስጥ ተገቢውን የመንገድ አጠቃቀም ደንብ በመተላለፋቸው ለቅጣት ከተዳረጉ 37 ሺህ እግረኞች መካከል 16 ሺህ የሚሆኑት በማህበራዊ አገልግሎት እንዲቀጡ መደረጉን የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን ለመናኸሪያ ሬዲዮ አስታውቋል።
የማህበራዊ አገልግሎት ቅጣቱ አትክልቶችን ውሃ ማጠጣት፣ አካባቢን ማጽዳት፣ አረጋውያንና ተማሪዎችን መንገድ ማሻገር እንዲሁም የተለያዩ ማህበራዊ አገልግሎቶችን ያካተተ መሆኑን የባለስልጣኑ የህዝብ ግንኙነት እና ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር ወይዘሮ ገነት ዲባባ ገልጸዋል።
የትራፊክ ህጎችን ያላከበሩ 21 ሺህ 202 እግረኞች ከማህበራዊ አገልግሎት ቅጣቱ በተጨማሪ ከ100 እስከ 150 ብር የሚደርስ የገንዘብ ቅጣት እንደተጣለባቸው አንስተው፤ እግረኞች የባለስልጣኑን ደንብ በማክበር ራሳቸውን ከትራፊክ አደጋ እንዲጠብቁ አሳስበዋል።
የህብረተሰቡን ግንዛቤ ከማሳደግ አንጻር በተለያዩ መንገዶች ለ15 ሚሊዮን ሰዎች የመንገድ ደህንነት ትምህርት ተደራሽ መሆኑን ገልጸዋል። በተጨማሪም በትራፊክ ቁጥጥርና ደንብ ማስከበር ስራዎች ትክክለኛ የመንገድ አጠቃቀም ያልተከተሉ ከ361 ሺህ በላይ አሽከርካሪዎች ላይ የእርምት እርምጃ መወሰዱ ተጠቁሟል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ