ሚያዚያ 12 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ)የጃፓን ባህር ኃይል የጦርነትን ታሪክ ሊቀይር የሚችል እና ሰው አልባ አውሮፕላኖችን በአየር ላይ እያሉ የማውደም አቅም ያለው እጅግ ዘመናዊ የሌዘር መሣሪያ ሙከራ መጀመሩን አስታውቋል።
ይህ 6,200 ቶን በሚመዝን የጦር መርከብ ላይ የተገጠመው ቴክኖሎጂ አሥር የ10 ኪሎ ዋት ሌዘር ጨረሮችን በአንድ ላይ በማቀናጀት 100 ኪሎ ዋት የሚመዝን እጅግ ኃይለኛ ጨረር በአንድ ነጥብ ላይ እንዲያርፍ ያደርጋል። ይህ ያተኮረ ኃይል ማንኛውንም የብረት አካል በአየር ላይ እያለ ለማቅለጥና የጥቃት ድሮኖችንም ሆነ የሚወረወሩ መድፎችን ለማክሸፍ የሚያስችል ከፍተኛ ብቃት አለው።
ከሌሎች የሚሳኤል መከላከያ መሣሪያዎች በተለየ መልኩ ይህ የሌዘር ሥርዓት ጥይት ወይም ሚሳኤል ማከማቻ አያስፈልገውም። መሣሪያው ኤሌክትሪክ እስካገኘ ድረስ ያለማቋረጥ መተኮስ የሚችል ሲሆን ይህም “ወሰን የሌለው ጥይት” ያለው ብቸኛው የጦር መሣሪያ ያደርገዋል። በተጨማሪም አንድን ሚሳኤል ለመተኮስ ከሚወጣው በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር ይልቅ ይህ መሣሪያ በአንድ ጥይት የሚያወጣው ወጪ እጅግ በጣም አነስተኛ መሆኑ ለሀገሪቱ የመከላከያ በጀት ትልቅ እፎይታ እንደሚሰጥ ተነግሯል።
ከየካቲት 20 ቀን 2018 ዓ.ም (February 27, 2026) ጀምሮ በሚደረገው የባህር ላይ ሙከራ መሣሪያው በከፍተኛ ንፋስ፣ በእርጥበትና በጨዋማ የባህር አየር ሁኔታ ውስጥ ያለውን ብቃት እንደሚፈተሽ ታውቋል። ጃፓን ይህንን ፕሮግራም በይፋ በማስጀመሯ እንደ አሜሪካ እና እንግሊዝ ያሉ ዘመናዊ የጨረር መሣሪያዎችን ወደ ተግባር ከቀየሩ ጥቂት የዓለም ሀገራት ተርታ ተቀላቅላለች።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ