ሚያዚያ 06 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ)ዲዲየር ዴሻምፕ ከ2026 የዓለም ዋንጫ በኋላ የፈረንሳይ ብሄራዊ ቡድንን እንደሚለቁ ማረጋገጣቸውን ተከትሎ፣ የሪያል ማድሪድ ቀጣይ አሰልጣኝ ለመሆን በክለቡ እጩ ዝርዝር ውስጥ መካተታቸው ተሰምቷል። አር ኤም ሲ ስፖርት (RMC Sport) እንደዘገበው ማድሪድ የዴሻምፕን ከፍተኛ ተጫዋቾችን የማስተናገድ ብቃት እና በታላላቅ መድረኮች ላይ ያለውን የውጤታማነት ታሪክ በአዎንታዊ መልኩ ተመልክቶታል። በተለይም አሰልጣኙ ስፓኒሽ ቋንቋ መናገራቸው እና እንደ ኪሊያን ምባፔ፣ ካማቪንጋ እና ኦሬሊየን ቹአሜኒ ካሉ የቡድኑ ኮከቦች ጋር ያላቸው የጠበቀ ግንኙነት ለማድሪድ ቤት ተመራጭ ያደርጋቸዋል።
በአሁኑ ወቅት ሻቢ አሎንሶን ተክቶ በጊዜያዊነት ቡድኑን እየመራ የሚገኘው አልቫሮ አርቤሎዋ በፕሬዝዳንት ፍሎሬንቲኖ ፔሬዝ ዘንድ ትልቅ ክብር ያለው ቢሆንም፣ የረጅም ጊዜ ቆይታው ግን በዚህ የውድድር ዘመን በሚያስመዘግበው ውጤት ላይ የተመሰረተ ይሆናል። አርቤሎዋ ትልቅ ዋንጫ ማሳካት ካልቻለ ዴሻምፕ በክረምቱ ክለቡን የመረከብ ሰፊ ዕድል አላቸው። ዲዲየር ዴሻምፕ ክለብ ካሰለጠኑ 14 ዓመታት ያለፉ ቢሆንም፣ በመጨረሻው የማርሴይ ቆይታቸው በሶስት ዓመታት ውስጥ ስድስት ዋንጫዎችን በማንሳት ስኬታማ ታሪክ ነበራቸው።
ክለቡ በአሁኑ ወቅት በላሊጋው ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ የሚገኝ ሲሆን፣ ከአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የሩብ ፍፃሜ ጨዋታ በሜዳው ተሸንፏል። በመሆኑም ማድሪድ ለተከታታይ ሁለተኛ ዓመት ያለ ዋንጫ የውድድር ዘመኑን ሊያጠናቅቅ የሚችልበት ዕድል ሰፊ መሆኑ እየተገለጸ ይገኛል። በዴሻምፕ ምርጫ ላይ የኪሊያን ምባፔ ፍላጎት ሳይኖርበት እንደማይቀርም ይገመታል።
የኪሊያን ምባፔን ስታቲስቲክስ በተመለከተ፣ በዘንድሮው የ2018 (2025/26) የውድድር ዘመን በሁሉም ውድድሮች (ለሪያል ማድሪድ እና ለፈረንሳይ ብሄራዊ ቡድን) ያስቆጠረው ግብ 43 ሲሆን 8 አመቻችቶ ማቀበል (assist) ችሏል። በሻምፒዮንስ ሊግ ብቻ ባደረጋቸው 10 ጨዋታዎች 14 ግቦችን ማስቆጠር የቻለ ሲሆን፣ በላሊጋው ደግሞ በ25 ጨዋታዎች 23 ግቦችን እና 4 አሲስቶችን አስመዝግቧል። ምንም እንኳን ተጫዋቹ በግሉ ድንቅ ብቃቱን እያሳየ ቢሆንም፣ ቡድኑ ባለፉት ሶስት ተከታታይ ጨዋታዎች ድል ባለመቀናቱ በአሰልጣኝ አልቫሮ አርቤሎዋ ላይ ያለው ጫና እየጨመረ መጥቷል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ