መጋቢት 16 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ)ሪያል ማድሪድ እና ብራዚላዊው ኮከብ ቪኒሲየስ ጁኒየር በኮንትራት ማራዘሚያ ጉዳይ ላይ ከረጅም ጊዜ ድርድር በኋላ ስምምነት ላይ መድረሳቸው ተረጋግጧል። ሁለቱ ወገኖች ላለፈው አንድ ዓመት ገደማ ሲደራደሩ የቆዩ ቢሆንም፣ በተለያዩ ምክንያቶች ስምምነቱ ሳይሳካ መቆየቱ ይታወሳል።
በዚህ አዲስ ስምምነት መሰረት ተጫዋቹ እስከ ሰኔ 2030 ድረስ በሳንቲያጎ በርናባው ለመቆየት የተስማማ ሲሆን፤ ይህም ቀደም ሲል በ2027 ያበቃ የነበረውን ውል በሦስት ተጨማሪ ዓመታት የሚያራዝም ይሆናል። ቪኒሲየስ በአዲሱ ውል መሰረት በዓመት 20 ሚሊዮን ዩሮ የተጣራ ክፍያ የሚያገኝ ሲሆን፣ ይህም በክለቡ ውስጥ ከፍተኛ ተከፋይ ከሆኑ ተጫዋቾች ተርታ ያሰልፈዋል።
ሪያል ማድሪድ ይህንን ውሳኔ ያሳለፈው በተለይም ከሳውዲ አረቢያ ክለቦች የሚቀርቡ ከፍተኛ የዝውውር ጥያቄዎችን ውድቅ ለማድረግ እና ተጫዋቹ የክለቡ የረጅም ጊዜ የአጥቂ ክፍል ዋና ተዋናይ መሆኑን በማረጋገጥ፣ ተረጋግቶ እንዲቆይ ለማድረግ ነው።
በዘንድሮው የ2025/26 የውድድር ዘመን ቪኒሲየስ ጁኒየር በሪያል ማድሪድ ቤት በሁሉም ውድድሮች 36 ጨዋታዎችን አድርጎ 22 ግቦችን በማስቆጠር እና 14 ኳሶችን አመቻችቶ በማቀበል እጅግ አስደናቂ ብቃት ላይ ይገኛል። ተጫዋቹ በላሊጋው 86 በመቶ የተሳካ የኳስ ቅብብል ስኬት ያለው ሲሆን፣ በአማካይ በጨዋታ 3.2 ስኬታማ ድሪብል እንዲሁም 2.1 ቁልፍ ኳሶችን ለቡድን አጋሮቹ ያቀርባል።
ይህ አዲስ የኮንትራት ስምምነት እጅግ ከፍተኛ የውል ማፍረሻ (Release Clause) ያካተተ ሲሆን፣ ይህም ሌሎች ክለቦች ተጫዋቹን በቀላሉ እንዳይወስዱት ትልቅ አጥር እንደሚሆን ይጠበቃል። ቪኒሲየስ ጁኒየር በባሎን ዶር ሽልማትም ከፍተኛ ግምት ከተሰጣቸው ተጫዋቾች አንዱ በመሆኑ፣ ይህ ውል በሪያል ማድሪድ ያለውን ቁልፍ ተፅዕኖ ይበልጥ የሚያጠናክረው ይሆናል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ