👉የትምህርት ፈተናዎችና ምዘና አገልግሎት በበኩሉ በሃገር አቀፍ ደረጃ የኮምፒውተር ድጋፍ ሰጪ ቡድን አቋቁሞ ችግሩን ለመፍታት እየሰራ መሆኑን ገልጿል::
በሞዴል ፈተና ወቅት የፈተና መፈተኛው ኤግዛም ሶፍትዌር በየኮምፒውተሩ ባለመጫኑ ምክንያት ቀልጣፋ አገልግሎትን ማግኘት እንዳልቻሉ የገለጹት አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የግል ትምህርት ቤት ዳይሬክተር በኢትዮጵያ ሙያና ቴክኒክ ኢንስቲትዩት ውስጥ ተማሪዎቻቸውን ሞዴል ፈተና ለማስፈተን እንደመጡና ኤግዛም ሶፍትዌር ባለመጫኑ ምክንያት በሚፈልጉት ጊዜ መፈተን እንዳልቻሉ ለመናኸሪያ ሬዲዮ ተናግረዋል፡፡
በኮምፒውተር ደረጃ ዘመኑን የሚመጥኑ ኮምፒውተሮችን ማየት እንደቻሉና በብዛትም ቢሆን በቂ እንደሆነ የሚገልጹት ዳይሬክተሩ፣ ነገር ግን ፈተናውን በትክክል ለማስኬድ ኤግዛም ሶፍት ዌሩ በጥንቃቄ እውቀት ባላቸው ባለሙዎች መጫን እንዳለበት ተናገረዋል፡፡
የትምህርት ቤቱ ዳይሬክተር አክለውም በበየነ መረብ ማስፈተን በዚህ አመት የመጀመሪያቸው እንደሆነና በትምህርት ቤቱ በኩል በቂ የስነ- ልቦናና የኮምፒውተር ልምምድ እንዳደረጉም ገልጸዋል፡፡ ተወዳዳሪና ወደፊትም ሀገርን የሚያስጠራ ተማሪን ለማፍራት በበየነ መረብ መሰጠቱ መልካም መሆኑን ገልጸው ነገር ግን ሲስተሙ አለመጫኑ ለፈተናው እንቅፋት እንዳይሆን ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡
ጉዳዩን አስመልክቶ ጣቢያችን ያነጋገራቸው በኢትዮጵያ የትምህርት ፈተናዎችና ምዘና አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ተፈራ ፈይሳ የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩቱን ጨምሮ አንዳንድ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሲስተሙን ሙሉ በሙሉ ያላስጫኑ እንዳሉና በማስጫን ሂደት ላይ መሆናቸዉን አምነዋል፡፡
አቶ ተፈራ፣ ይህ ክፍተት በክልልና በዞን ደረጃም ሊከሰት ስለሚችል ተቋሙ በሃገር አቀፍ ደረጃ የኮምፒውተር ድጋፍ ሰጭ ቡድን አቋቁሞ ችግሩን ለመፍታት እየሰራ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡
በኢትዮጵያ በተያዘው አመት ለሁለተኛ ጊዜ የሚሰጠውን የበየነ መረብ የፈተና አሰጣጥ ከባለፈው አመት ልምድ በመውሰድ በተሻለ መልኩ ብዛት ያላቸው ተማሪዎችን ለመፈተን ዝግጅት እየተደረገ እንደሆነ አቶ ተፈራ አመላክተዋል፡፡
ምላሽ ይስጡ