ጥቅምት 28 ቀን 2019(መናኸሪያ ሬዲዮ) በአሁኑ ጊዜ በመንገዶቻችን ላይ የኤሌክትሪክ መኪኖች (EVs) በብዛት ማየት የተለመደ ሆኗል።
የኤሌክትሪክ መኪና ሲኖረን የነዳጅ መኪና ላይ እንደምናደርገው ዘይት መቀየር፣ ፕለግ ማፅዳት ወይም የሞተር ጥገና የለም ብለን ልንዘናጋ እንችላለን። ነገር ግን ፍፁም ጥገና አያስፈልጋቸውም ማለት አይደለም!
መኪናችን ለብዙ ዓመታት በሙሉ አቅሙ እንዲያገለግለን እና የመኪናው ውዱ አካል የሆነው ባትሪ እንዳይበላሽብን እነዚህን 4 ቀላል ነገር ግን ወሳኝ ጥንቃቄዎች ማወቅ አስፈላጊ ነው።
የመጀመሪያውና ዋናው ነገር የባትሪ ቻርጅ አጠቃቀማችን ነው። ባትሪው ሙሉ በሙሉ 0% እስኪሆን አቃጥሎ መጠቀምም ሆነ ሁልጊዜ 100% ሞልቶ ረጅም ጊዜ እንዲቆይ ማድረግ ዕድሜውን በእጅጉ ያሳጥራዋል።
የመኪና ባለሙያዎች የሚመክሩት የባትሪውን መጠን ሁልጊዜ ከ20% እስከ 80% ባለው ክልል ውስጥ አቆይቶ መጠቀም የባትሪውን ጤንነት ለረጅም ጊዜ እንደሚጠብቅ ነው።
ሁለተኛው የብሬክ ሲስተም ፍተሻ ነው። የኤሌክትሪክ መኪኖች ፍጥነት ሲቀንሱ ኃይል ወደ ባትሪው የሚመልስ (Regenerative braking) ቴክኖሎጂ ስላላቸው የብሬክ ፓዳቸው በፍጥነት አይበላሽም።
ነገር ግን ይህ ማለት የብሬክ ዘይት እና የዲስክ አቧራ ፍተሻ አያስፈልግም ማለት ስላልሆነ በየጊዜው ማሳየት ተገቢ ነው።
ሶስተኛው ደግሞ የባትሪ ማቀዝቀዣ ፈሳሽ (Coolant) ነው። ባትሪዎች በሚሞሉበትም ሆነ ረጅም መንገድ በሚነዱበት ጊዜ ከፍተኛ ሙቀት ያመነጫሉ።
ይህንን ሙቀት የሚቆጣጠረው ማቀዝቀዣ ፈሳሽ መጠኑ በቂ መሆኑን እና መፍሰስ አለመኖሩን ዘወትር ማረጋገጥ መኪናውን ከከፍተኛ አደጋ ይታደጋል።
አራተኛውና አብዛኛው ሰው ትኩረት የማይሰጠው የጎማ እንክብካቤ ነው። የኤሌክትሪክ መኪኖች ባትሪ ስላላቸው ከተራ መኪና በክብደት ይበልጣሉ፤ በተጨማሪም ረገጥ ስናደርጋቸው የሚሰጡት ድንገተኛ ከፍተኛ ጉልበት (Instant Torque) ጎማቸው በፍጥነት እንዲያልቅ ያደርገዋል።
ስለዚህ የጎማ አየር ግፊትን በየጊዜው ማስተካከል እና ጎማዎችን ቦታ ማቀያየር (Rotation) ማድረግ የጎማውን ዕድሜ ያራዝማል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ