ጥቅምት 26 ቀን 2019(መናኸሪያ ሬዲዮ) የቤት ግንባታ ሲታሰብ ቀድሞ ወደ አእምሯችን የሚመጣው የሲሚንቶ፣ አሸዋ እና ድንጋይ ውህደት ነበር። ነገር ግን ይህ ብዙ ጊዜና ከፍተኛ ወጪ የሚይዝ ባህላዊ አሰራር በአዲሱ የቴክኖሎጂ ፈጠራ በፍጥነት እየተተካ ይገኛል።
አሁን ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ መነጋገሪያ የሆነውና እንደ ህፃናት መጫወቻ (Lego) እርስ በእርስ የሚገጣጠመው የእንጨት ብሎኬት፣ የኮንስትራክሽን ዘርፉን አሰራር ሙሉ በሙሉ እየቀየረው ነው። ይህ ፈጠራ የተለመደውን የሲሚንቶ ብሎኬት በመተካት፣ ያለ ምንም ውኃ፣ አሸዋ እና ሲሚንቶ አጠቃቀም በደረቁ የቤት ግድግዳን በጥቂት ቀናት ውስጥ ሰርቶ ለማጠናቀቅ ያስችላል።
እነዚህ ብሎኬቶች በፋብሪካ ደረጃ በከፍተኛ ጥራት ከተቀነባበሩ እንጨቶች የተሰሩ ሲሆን፣ በውስጣቸው ሙቀትና ቅዝቃዜን የሚከላከል ቁሳቁስ ይዘው ይዘጋጃሉ። ብሎኬቶቹ እርስ በእርስ የሚቆለፉ በመሆናቸው አሰራራቸው የተወሳሰበ የግንባታ ሙያ አይጠይቅም። ቦታቸው ላይ ለማስቀመጥና ለማጠባበቅ የሚያስፈልገው የላስቲክ መዶሻ ብቻ ሲሆን፣ ከተደረደሩ በኋላ በውስጣቸው በሚያልፉ የእንጨት ወይም የብረት ዘንጎች እርስ በእርስ ተያይዘው የታሰሩ በመሆናቸው ለቤት ግድግዳ የሚሆን እጅግ ጠንካራ መዋቅር ይፈጥራሉ።
የዚህ ቴክኖሎጂ ጥቅሞች በርካታ ናቸው። በወራት የሚቆጠርን የኮንክሪትና የሲሚንቶ ማድረቂያ ጊዜ በማስቀረት፣ የአንድን ቪላ ቤት ሙሉ ግድግዳ ከሶስት እስከ አምስት ባሉት ቀናት ውስጥ ሰርቶ ለማጠናቀቅ ያስችላል። ከባድ ማሽነሪዎችን እና በርካታ የሰራተኛ ኃይልን ስለማይፈልግ የግንባታ ወጪን በከፍተኛ ደረጃ ይቀንሳል። በተጨማሪም የሲሚንቶ ምርት የሚያስከትለውን ከፍተኛ የካርበን ልቀት በማስቀረት ለአካባቢ አየር ንብረት ተስማሚ የሆነ አሰራርን ያቀርባል። በብሎኬቱ ውስጥ ያለው የመከላከያ ንብርብር በቤቱ ውስጥ ያለውን የሙቀት መጠን ስለሚቆጣጠር፣ ለቅዝቃዜና ለሙቀት ማሞቂያ የሚወጣውን የኤሌክትሪክ ኃይል ይቆጥባል ነው የተባለው።
በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የአውሮፓ ሀገራትና በአውስትራሊያ ለቪላዎች፣ ለተጨማሪ ክፍሎችና ለአነስተኛ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ በስፋት እየዋለ የሚገኘው ይህ ቴክኖሎጂ፣ ወደፊት የሲሚንቶን የበላይነት በከፊል ሊተካ እንደሚችል የዘርፉ ባለሙያዎች ይገምታሉ።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ