ጥቅምት 25 ቀን 2019(መናኸሪያ ሬዲዮ) ተቋማት በጋራ ኃላፊነት እንዲተገብሩት የወጣውን አዋጅ በማስፈጸም የሳይበር ደህንነትን እንዲያስጠብቁ ልዩ ክትትል እንደሚደረግ በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የኢንፎርሜሽን ኢንሹራንስ ዘርፍ ምክትል ኃላፊ ዶክተር ጥላሁን እጅጉ ለመናኸሪያ ሬዲዮ ተናግረዋል።
ተቋማት የሳይበር ደህንነትን የመጠበቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው የጠቀሱት ኃላፊው፤ በተለይ ተደጋጋሚ ጥቃት የሚሞከርባቸው የፋይናንስ ተቋማት በመሆናቸው ከብሔራዊ ባንክ ጋር በጋራ እንደሚሰራ ገልጸዋል።
በተናጠል ባንኮች የሚጠቀሙበትን ሲስተም በመከታተልና በመፈተሽ ቁጥጥር እንደሚደረግም ተናግረዋል።
ተቋማት አሁንም የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት በብቃት እየተወጡ እንዳልሆነ ገልጸው፤ በዚህም ምክንያት «ክሪቲካል ኢንፍራስትራክቸር» የሚባል አዋጅ ከዚህ ቀደም ጸድቆ ወደ ሥራ መገባቱን አብራርተዋል።
በአዋጁ ተቋማት በቂ ባለሙያ የመቅጠር፣ ሥጋትን ቀድሞ ተንብዮ የመከላከል እና ለደንበኞች የማሳወቅ ኃላፊነት እንደተካተተበት ገልጸዋል።
አሁን ላይ ተቋማት በሚጠበቀው ልክ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ባይሆንም፤ በተቀመጠው የጋራ ደንብና አዋጅ መሠረት ክትትል እየተደረገ ተጠያቂ የማድረጉ ሥራ በዚያው ልክ እንደሚሠራ ኃላፊው አክለዋል።
የፋይናንስ ተቋማትም ሆኑ ሌሎች ተቋማት፤ የደንበኞቻቸውን እና የአገልግሎታቸውን ደህንነት ለማስጠበቅ አዋጁን በአግባቡ መተግበር እንዳለባቸው ኃላፊው አስገንዝበዋል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ