ጥቅምት 17 ቀን 2019(መናኸሪያ ሬዲዮ) የአየር ንብረት መበላሸት ያስከተለው የኡደት መዛባት ወቅቶች የጠበቁትን የዝናብና የፀሐይ መጠን በማሳጣት ለድንገተኛ ጎርፍ፣ ለተደጋገመ ድርቅ እና በረሃማነት መንስኤ መሆኑ ተመላክቷል። ይህን ተከተሎም እንደ መተንፈሻ አካል ያሉ የተለመዱ የጤና እክሎች በስፋት እንደሚከሰቱና የሚያደርሱትም ጉዳት ከፍተኛ እንደሚሆን ተገልጿል። የአየር ንብረት መዛባቱ ቀጥተኛ የበሽታዎች ምንጭ ባይሆንም፣ የሚከሰቱ የጤና ችግሮች እንዲባባሱ አጋዥ ምክንያት መሆኑን በጤና ሚኒስቴር የህዝብ ጤና እና የአካባቢ ጤና አጠባበቅ ከፍተኛ ባለሙያው አቶ አሽረፈዲን ዮያ አስረድተዋል።
በሌላ በኩል ላለፉት 35 ዓመታት በስነተዋልዶ ጤና ዘርፍ ሲሰራ የቆየው ኤም ኤስ አይ ኢትዮጵያ ረፕሮዳክቲቭ ቾይስ፤ ከአካባቢ መራቆት ጋር ተያይዞ የሚፈጠር ፍልሰት ማህበራዊ ጫናዎችን እየጨመረ መምጣቱን ጠቁሟል። በተለይም በፍልሰት ላይ ካሉ ዜጎች መካከል አብዛኞቹ ሴቶችና ህፃናት በመሆናቸው፣ በጉዟቸው ወቅት ለተለያዩ ፆታዊ ጥቃቶች፣ ከትምህርት ገበታ መራቅ፣ ለበሽታዎች መጠቃት እና ለስነተዋልዶ ጤና አገልግሎቶች መስተጓጎል እንደሚዳረጉ የድርጅቱ ሰነዶች ያመለክታሉ።
እነዚህን ችግሮች ለመቋቋም የሚያስችል የጋራ አሰራር እና ስትራቴጂ ተቀርጾ ወደ ትግበራ መገባቱን አቶ አሽረፈዲን ዮያ ገልጸዋል። ከዚህ ጎን ለጎን “ግሪን ሄልዝ አፍሪካ” የተባለ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ከወጣት ድምፅ መድረክ ጋር በመተባበር የወጣቱን ክፍል ማዕከል ያደረገ የምክክር መድረክ አዘጋጅቷል። ይህም ትልቁን የህብረተሰብ ቁጥር የሚይዘው ወጣት ክፍል የአየር ንብረት ለውጥ ያመጣቸውን የረሃብ፣ የፍልሰት እና የጤና ስጋቶች ተቋቁሞ መፍትሔ አመንጪ እንዲሆን ለማስቻል የታለመ መሆኑ ተመልክቷል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ