ነሐሴ 25 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ) የኤልኒኖን ተጽዕኖ ለመቆጣጠር በግድቦች የውሃ አያያዝ እና አስተዳደር ላይ እየተሰራ መሆኑን ለመናኸሪያ ሬዲዮ ያስታወቁት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኃይል ማመንጨት ቢዝነስ ዩኒት ምክትል ስራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ኤፍሬም ወ/ኪዳን ናቸው። ኢትዮጵያ ከፍተኛ የውሃ መጠን የምታገኘው ከሀምሌ እስከ ጥቅምት ባሉት አራት ወራት መሆኑን የገለጹት ኢንጂነር ኤፍሬም፣ በተጠቀሱት ጊዜያት ከ80 በመቶ በላይ የውሃ መጠን እንደሚገኝ ተናግረዋል። አሁን ላይ የነሐሴ ወር እየተጠናቀቀ ቢሆንም፣ አስቀድሞ ከሀምሌ ወር ጀምሮ በግድቦች የውሃ ይዘት አስተዳደር ላይ ክትትል ሲደረግ መቆየቱን እና ይህም ስራ እስከ ጥቅምት ወር ማብቂያ እንደሚቀጥል ገልጸዋል። እንደ ሀገር 97 በመቶ የሚሆነው ኃይል የሚመነጨው ከውሃ በመሆኑ፣ የኤልኒኖን ተጽዕኖ ለመቋቋም አስቀድመው ብዙ የውሃ መጠን ያገኙትን ግድቦች በመቆጣጠር፣ ውሃ ያልያዙ ግድቦች ደግሞ በቂ ውሃ የሚይዙበትን አሰራር በመቀየስ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን አክለዋል። ተቋሙ ከመጋቢት ወር ጀምሮ በውሃ አያያዝ ላይ ሲሰራ እንደቆየ በመግለጽ፣ ሂደቱን በማስቀጠል በጥቅምት ወር መጨረሻ የሚኖረው ውጤት እንደሚገመገም ኢንጂነር ኤፍሬም ገልጸዋል። ከኤልኒኖ ተጽዕኖዎች መካከል ዋነኛው በዝናብ እጥረት ምክንያት የሚከሰት የውሃ መጠን መቀነስ እንደሆነ መገለጹ ይታወሳል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ