መስከረም 06 ቀን 2019ዓ.ም.(መናኸሪያ ) ትምህርት ቤቶች በሚከፈቱበት ጊዜ የትራንስፖርት እጥረቱን ለመፍታት ኮድ 3ን ጨምሮ በትምህርት ቤቶችና በወላጆች ፈቃድ የወሰዱ ተሽከርካሪዎች ተማሪዎችን በማመላለስ ሥራ እንዲሰማሩ መደረጉን ቢሮው ለጣቢያችን አስታውቋል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ በመስከረም ወር የአደባባይ በዓላትን ጨምሮ ትምህርት ቤቶች ሲከፈቱ በከተማዋ የትራንስፖርት አገልግሎት እጥረትና መስተጓጎል ስለሚጋጥም ይህንን ችግር ለመቅረፍ ቢሮው የተለያዩ ጥረቶችን በማድረግ ላይ መሆኑን የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ የኦፕሬሽን ዘርፍ ምክትል ኃላፊ አቶ ዳኛቸው ሽፈራው ለጣቢያችን ገልጸዋል፡፡ ትምህርት ሲከፈት በከተማዋ ውስጥ ከ1 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች እንቅስቃሴ ስለሚያደርጉ ይህም ከመደበኛ ሰራተኞች የስራ ሰዓት ጋር ተመሳሳይ ስለሆነ የትራፊክ ፍሰት መጨናነቅ፣ የታክሲና የብዙሃን ትራንስፖርት እጥረት እንደሚያጋጥም አክለው፤ ይህንንም ለማስተካከል ከዚህ በፊት የነበረውን ገደብ በዚህ ዓመት በማንሳት በሕጉ መሰረት አገልግሎት እንዲሰጡ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡ የተማሪዎች የኮንትራት ታክሲ አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎች ተማሪዎችን ብቻ በማመላለሳቸው የሕዝብ አገልግሎት የሚሰጡበት ሁኔታ እንዳይቀንስ ቢሮው ያስቀመጠው አቅጣጫ ተሽከርካሪዎቹ ተማሪዎቹን ከጠዋቱ 1 ሰዓት ከ30 ቅድመ-ሰዓት አድርሰው በተርሚናላቸው ውስጥ መገኘት እንዳለባቸው እንደሚያደርጉም ገልጸዋል፡፡ የተማሪ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎችና አውቶቡሶች በተጠቀሰው ሰዓት በቦታቸው መገኘታቸውን በተርሚናላቸው ውስጥ ከ1 ሰዓት ከ30 ደቂቃ በፊት በፊርማ ማረጋገጥ ስላለባቸው ይህንን የመቆጣጠር ሥራ በስፋት እንደሚሰራ ኃላፊው አስረድተዋል፡፡ የተሳለጠ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲኖር ወላጆች ልጆቻቸውን በጠዋቱ ወደ ትራንስፖርት ቦታ መላክ እንዳለባቸውም ገልጸዋል፡፡
___
ሀሳብ እና‘ሳ‘ፍራለን
ምላሽ ይስጡ