ነሐሴ 22 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ) የ26 ዓመቱ የእንግሊዝ የክንፍ መስመር ተጫዋች ሪስ ኔልሰን ከአርሰናል ጋር የነበረውን ውል በጋራ ስምምነት በማቋረጥ፣ ከአካዳሚ አንስቶ ካደገበት ክለብ ጋር በቋሚነት መለያየቱ ተሰምቷል። እስከ ሰኔ 2027 የሚቆይ ኮንትራት የነበረው ኔልሰን፣ ውሉ በጋራ ስምምነት እንዲቋረጥ በመደረጉ ምክንያት ያለ ምንም የዝውውር ክፍያ ወደ ፈለገው ክለብ የማመራት ነፃነት አግኝቷል። ይህ ስምምነት አርሰናል ለተጫዋቹ በሳምንት ይከፍለው የነበረውን 100 ሺህ ፓውንድ ደመወዝ ከወጪ መዝገቡ ላይ እንዲቀንስ ያስቻለው ሲሆን፤ ኔልሰን በቀጣይ ከእንግሊዝ እና ከሌሎች የአውሮፓ ክለቦች የሚቀርቡለትን ጥያቄዎች መዝኖ ቀጣይ ማደሪያውን እንደሚመርጥ ተገልጿል። በአርሰናል የዋናው ቡድን ቆይታው በሁሉም ውድድሮች በ90 ጨዋታዎች ተሰልፎ 8 ግቦችን ማስቆጠር ችሏል። በፕሪሚየር ሊጉ ብቻ በ50 ጨዋታዎች 4 ግቦችን እና 2 አሲስቶችን ያስመዘገበ ሲሆን፤ በተለይም በ2022-23 የውድድር ዘመን በርንመዝ ላይ ባለቀ ሰዓት ያስቆጠራት ድንቅ የማሸነፊያ ግብ የሊጉ የዓመቱ ምርጥ ልዩነት ፈጣሪ ክስተት (“Game Changer of the Season”) ተብላ መመረጧ የሚታወስ ነው። ኔልሰን እንደ ፉልሃም፣ ብሬንትፎርድ፣ ሆፈንሃይም እና ፌይኖርድ ባሉ ክለቦች በውሰት ካሳለፈ በኋላ፣ በቋሚነት አርሰናልን ለመልቀቅ መወሰኑ ተረጋግጧል። በቀጣይም መዳረሻው የትኛዉ ክለብ ይሆናል የሚለው ጉዳይ ይጠበቃል።
__ ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ