ነሐሴ 20 ቀን 2018 (መናኸሪያ ሬዲዮ) እንደ ESPN ዘገባ ከሆነ ሚኬል አርቴታ ተጫዋቹን አዲስ ክለብ እንዲፈልግ ቀጭን መልዕክት አስተላልፏል፤ አንዳንድ የአርሰናል ተጫዋቾች እና የቡድን አጋሮቹ በአሰልጣኙ ንግግር ማዘናቸውን እና ደስተኛ አለመሆናቸውን አሳውቀዋል ሲል ዘግቧል።
ተጫዋቹ በኮሚኒቲ ሺልድ መርሃ ግብር ላይ ከስብስቡ ውጪ እንዲሆን የተደረገበት መንገድ ሜዳሊያ እንኳን እንዳያገኝ ያደረገው ሲሆን፣ ያ ደግሞ የቡድን አጋሮቹን ደስተኛ እንዳላደረገ ተነግሯል። መድፈኞቹን ረዘም ላለ ጊዜ ካገለገሉ ተጫዋቾች መካከል ማርቲኔሊ አንዱ እና ዋነኛው ነው።
የባህረ ሰላጤው ክለብ አል ሂላል ጋብሪኤል ማርቲኔሊን ለማስፈረም እንቅስቃሴ መጀመሩን ለማወቅ ተችሏል። አርሰናል ከተጫዋቹ እስከ 60 ሚሊዮን ፓውንድ እንዲቀርብለት እንደሚፈልግ የሚጠቁሙ መረጃዎች ቢወጡም፣ አል ሂላሎች ግን ከዛ ዝቅ ባለ የዝውውር ሂሳብ ዝውውሩን ለማጠናቀቅ እንደሚሰሩ ተጠቁሟል።
አሁን ባለው ወቅታዊ ሁኔታ አል ሂላሎች ተጫዋቹን ለማስፈረም ከክለቡ አርሰናልም ሆነ ከተጫዋቹ ጋር በግል ጥቅማጥቅሞች ዙሪያ እየተነጋገሩ እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል።
የ25 ዓመቱ ብራዚላዊ አጥቂ በተጠናቀቀው የ2025/26 የፕሪሚየር ሊግ ውድድር ዘመን ለአርሰናል የተጫወተው 1000 ደቂቃዎችን ያህል ብቻ ሲሆን፣ በሊጉ ማስቆጠር የቻለው አንድ ግብ ብቻ ነው። ሆኖም ግን በቻምፒየንስ ሊጉ 6 ግቦችን ማስቆጠር የቻለ ሲሆን፣ ክለቡ ከ2004 በኋላ በአውሮፓ መድረክ ትልቁን እና የተሳካውን ጉዞ እንዲጓዝ የራሱን አስተዋጽኦ አበርክቷል። በቅርቡ በተጠናቀቀው የዓለም ዋንጫ ከሀገሩ ብራዚል ብሔራዊ ቡድን ጋር በነበረው ቆይታ በቅድመ ጥሎ ማለፍ ጨዋታ ጃፓን ላይ በተጨማሪ ደቂቃ ላይ ወሳኝ የማሸነፊያ ግብ ማስቆጠሩ ይታወሳል።
ክርስቶስ ጾሊስ ወደ መድፈኞቹ ካምፕ መቀላቀሉን ተከትሎ የማርቲኔሊ ቀጣይ ማረፊያ በባህረ ሰላጤው ሊግ የሚጫወተው ክለብ አል ሂላል የመሆን ዕድሉ ሰፍቷል።
ማርቲኔሊ በአርሰናል በዓመት 7 ሚሊዮን ዩሮ የሚያገኝ ሲሆን፣ ተጫዋቹ ከሰሜን ለንደኑ ክለብ ጋር ያለው ውል እስከ 2027 የሚያቆየው ቢሆንም አርሰናል ውሉን ለተጨማሪ አንድ ዓመት የማራዘም አማራጭ አለው። ሆኖም ግን በዚህ የክረምት የዝውውር መስኮት ክለቡን ለቆ ሊወጣ የሚችልበት ዕድል ሰፊ ስለመሆኑ ተዘግቧል።
የእንግሊዙ ፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዮን አርሰናል በዚህ የክረምት የዝውውር መስኮት የመስመር አጥቂውን ሌአንድሮ ትሮሳርድን ለቱርኩ ቤሺክታሽ አሳልፎ ከሰጠ በኋላ ሌላኛውን ብራዚላዊ የክንፍ መስመር ተጫዋች ገብርኤል ማርቲኔሊን ለሽያጭ ማቅረቡን ተከትሎ፣ አል ሂላልን ጨምሮ አራት ታላላቅ ክለቦች ተጫዋቹን ለማስፈረም ፍላጎት ማሳየታቸውን ትራንስፈር ማርኬት ዘግቧል።
የ25 ዓመቱ ብራዚላዊ ኮከብ በአሁኑ ወቅት በገበያው ላይ 45 ሚሊዮን ዩሮ የሚገመት የዝውውር ዋጋ ያለው ሲሆን፣ ባለፈው የውድድር ዘመን በፕሪሚየር ሊጉ ማሳየት ከነበረበት ብቃት በታች በመገኘቱ እና በ30 ጨዋታዎች ላይ 1 ጎል ብቻ ማስቆጠር በመቻሉ በአሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ ስር የመደበኛ ቋሚ ተሰላፊነት ቦታውን አጥቷል። ይህ ቢሆንም የማርቲኔሊ በሜዳ ላይ ያለው ከፍተኛ ፍጥነት፣ ትጋት እና የመከላከል እገዛ አሁንም በተለያዩ ክለቦች እንዲፈለግ እና ተመራጭ ያደርገዋል።
ተጫዋቹ በ2019 ከብራዚል 4ኛ ታችኛው ዲቪዥን ክለብ በ6 ሚሊዮን ዩሮ ነበር አርሰናልን የተቀላቀለው። በአጠቃላይ በሁሉም ውድድሮች ለመድፈኞቹ 300 በሚጠጉ መርሃ ግብሮች ላይ ተሰልፎ ተጫውቷል። ላለፉት 2 ዓመታት አቋሙ እየወረደ ቢሄድም እንኳ፣ ዘንድሮ የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ የቡድኑ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ሆኖ ማጠናቀቅ ችሏል።
በከፍታም ሆነ በዝቅታ ጊዜ ለክለቡ የነበረው አስተዋጽኦ እጅግ የማይዘነጋ ነው በሚል በተጫዋቹ ጉዳይ የተሰማቸውን ሀዘን በዚህ መልኩ እየገለጹ የሚገኙ የክለቡ ደጋፊዎች አልጠፉም።
ገብርኤል ማርቲኔሊ እ.ኤ.አ በ2019 አርሰናልን ከተቀላቀለ ጀምሮ በሁሉም ውድድሮች በአጠቃላይ በ278 ጨዋታዎች ላይ መሰለፍ የቻለ ሲሆን፣ በእነዚህም ጨዋታዎች 62 ጎሎችን ከመረብ ማረፍ ችሏል። በፕሪሚየር ሊጉ ብቻ 191 ጨዋታዎችን አድርጎ 41 ጎሎችን እና 24 ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን ያመቻቸ ሲሆን፣ በቆይታውም የፕሪሚየር ሊግ፣ የኤፍ ኤ ካፕ እና የኮሚዩኒቲ ሺልድ ዋንጫዎችን ከለንደኑ ክለብ ጋር በጋራ ማሸነፍ ችሏል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ