ሰኔ 23 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ውይይትና ምክክር ሲያደርግባቸው ከቆየባቸው አጀንዳዎች መካከል የሕፃናት ጉዳይ እንደሚገኝበት ቀደም ሲል መግለጹ ይታወቃል። ይህንኑ ተከትሎ ኮሚሽኑ የመጨረሻ ባላቸው 8 ዋና ዋና አጀንዳዎች ውስጥ የሕፃናት አጀንዳ በስም ተጠቅሶ ለምን አልተቀመጠም ሲል ጣቢያችን ኮሚሽኑን ጠይቋል።
ሕፃናትን በሚመለከት በምክክር ሂደቱ ውስጥ በሙሉ እንደ አጀንዳ ሐሳብ ሲነሳ የቆየ መሆኑን በመጥቀስ፣ አሁን ላይ የመጨረሻ በተባሉት ስምንት አጀንዳዎች ውስጥ ስለመካተቱ ዋና ኮሚሽነሩ ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ለመናኸሪያ ሬዲዮ ተናግረዋል።
በመሆኑም የሕፃናት ጉዳይ በስም ለብቻው ባይጠቀስም፣ በአጀንዳ ቁጥር 5 ንዑስ ቁጥር 5.1.3 “አካል ጉዳት፣ ተጋላጭና የተገለሉ ቡድኖች መብቶች” በሚለው ሥር መካተቱን ዋና ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።
በተለይ ሕፃናት በተለያዩ ጊዜያት በሚፈጸሙ ግጭቶችና ጦርነቶች ውስጥ ቀዳሚ ሰለባ መሆናቸው ይታወቃል ያሉት ዋና ኮሚሽነሩ፤ በመሰል ሂደቶች ውስጥ ለችግር ይበልጥ ተጋላጭ በመሆናቸው ምክንያት፣ አጀንዳዎቻቸው “ተጋላጭና የተገለሉ ቡድኖች” በሚለው ሥር እንደሚጠቃለልና በዚያው ሥር እንደሚታይ አስረድተዋል።
በመጨረሻዎቹ 8 ወሳኝ የሚባሉ ዋና ዋና አጀንዳዎች ውስጥ ለብቻው በስም ባይጠቀስም፣ የወጣቶችም ጉዳይ በተመሳሳይ በሌሎች ስያሜዎች አብሮ መጠቀሱን ፕሮፌሰር መስፍን ጠቅሰዋል።
በስም ያልተጠቀሱ በርካታ ተናጥላዊ ጉዳዮች እንደ ጥያቄ ሊቀርቡ ቢችሉም፣ የመጨረሻ ተብለው በቀረቡት ዋና ዋና አጀንዳዎች ውስጥ ያልተካተተ ሐሳብ የለም ሲሉ ዋና ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ