ሰኔ 18 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ) አብርሆት ስፔሻላይዝድ የሳይኮሎጂ ማዕከል ከለርኒንግ ሊንክ አፍሪካ፣ ከኬንያታ ዩኒቨርሲቲ፣ እንዲሁም ከሌሎች ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር “ወላጆችን ማብቃት፣ አካታች ትምህርትን ማሳደግ፤ ከግንዛቤ ወደ ተግባር” በሚል መሪ ቃል በኢትዮጵያ የኦቲዝም እና የትምህርት እክል ያለባቸውን ተማሪዎች ለመደገፍ የሚያስችል ጉባኤ አካሂዷል።
ጉባኤው በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚገኙ የነርቭ ዕድገት ልዩነት ላለባቸው ሕፃናት ምቹ ማዕቀፍ ለመዘርጋት የታለመ መሆኑን የገለጹት የዓብርሆት ስፔሻላይዝድ የሳይኮሎጂ ማዕከል ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር ኤዶሚያስ ደጀኔ፤ ምንም እንኳን አካታች የትምህርት ፖሊሲዎች በወረቀት ላይ ቢኖሩም፣ በተግባር እየተሠራባቸው አለመሆኑን አንስተዋል። በዚህም ምክንያት ከ60 በመቶ በላይ የሚሆኑ ወላጆች ልጆቻቸው ሲቸገሩ የመርዳት አቅም እንደሌላቸውና ተስፋ የመቁረጥ ስሜት እንደሚሰማቸው ገልጸዋል።
ይህን ችግር ለመፍታት እየተከናወነ ካለው ሥራ በተጨማሪ፣ ወላጆች በልጆቻቸው ዙሪያ ያሉ ጉድለቶችን በተሻለ ሁኔታ መደገፍ እንዲችሉ የሚያግዝ መመሪያ መዘጋጀቱንም አስታውቀዋል።
መመሪያው የወላጆችን እና የቤተሰብን ጭንቀት ወደ ሙያዊ እና ትምህርታዊ ብቃት የሚቀይር፣ ባህልን ያገናዘበ ሥርዓትን የሚያመቻች መሆኑን ዋና ሥራ አስኪያጁ ጠቅሰው፤ መመሪያውን ለማኅበረሰቡ ተደራሽ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑንም አክለው ገልጸዋል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ