ግንቦት 20 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ) ኔዘርላንድስ ለመጪው የዓለም ዋንጫ ብሔራዊ ቡድኗን ይፋ ስታደርግ የባየር ሌቨርኩዘኑን ጄረሚ ፍሪምፖንግን ከስብስቡ ውጭ ማድረጓ አስገራሚ ሆኗል። የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ሮናልድ ኩማን ትላንት ከሰዓት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳረጋገጡት፣ አጥቂው ሜምፊስ ዲፓይ እና የአርሰናሉ ተከላካይ ዩሪየን ቲምበር የጉዳት ስጋት ቢኖርባቸውም በስብስቡ ውስጥ ተካተዋል። በ55 ጎሎች የሀገሪቱ የምንግዜም ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ የሆነው የ32 ዓመቱ ዲፓይ ከጭን እና ባት ጉዳት ጋር ሲታገል የቆየ ሲሆን፣ ባለፉት ሁለት ወራት ለብራዚሉ ክለቡ ቆሮንቶስ (ኮሪንቲያንስ) ተቀይሮ የገባው በሁለት ጨዋታዎች ላይ ብቻ መሆኑ ለጨዋታ ያለውን ዝግጁነት አጠያያቂ አድርጎታል።
በተመሳሳይ የ24 ዓመቱ ዩሪየን ቲምበር በቅርቡ ባጋጠመው ጉዳት ምክንያት በቡድኑ ውስጥ መካተቱ ሌላው ትኩረትን የሳበ ጉዳይ ሆኗል። ተጫዋቹ ባለፈው መጋቢት ወር ከኤቨርተን ጋር በነበረው ጨዋታ በብሽሽት ጉዳት ምክንያት ከሜዳ ከወጣ በኋላ ለክለቡ በሁሉም ውድድሮች 14 ጨዋታዎች ያመለጡት ሲሆን፣ በዚህ ሳምንት ወደ አርሰናል ልምምድ በመመለስ ቅዳሜ ለሚካሄደው የሻምፒዮንስ ሊግ የፍጻሜ ጨዋታ የተወሰነ ደቂቃ ሊያገኝ እንደሚችል ይገመታል።
በሌላ በኩል ባለፈው ጥር ወር ከጉልበት ቀዶ ጥገና ካገገመ በኋላ ለቦርንማውዝ በሁለት ጨዋታዎች ብቻ ተቀይሮ የገባው ጀስቲን ክላይቨርት እና በመጋቢት ወር ክለቡ ጋላታሳራይ ከሊቨርፑል ጋር በሻምፒዮንስ ሊግ ባደረገው ጨዋታ ያጋጠመውን የጣት ጉዳት ያገገመው ኖአ ላንግ በስብስቡ ውስጥ ተካተዋል።
የዌስትሃም ዩናይትዱ ክሪሴንሲዮ ሰመርቪል እና የሰንደርላንዱ ግብ ጠባቂ ሮቢን ሮፍስ ለመጀመሪያ ጊዜ ለብሔራዊ ቡድኑ ጥሪ ሲደረግላቸው፣ ማርተን ዴ ሮን ከሁለት ዓመታት በኋላ በድጋሚ ወደ መሃል ሜዳው ተመልሷል። በሌላ በኩል ኢንተር ሚላን ከቦሎኛ ጋር ባደረገው የሴሪአ የመጨረሻ ጨዋታ የጭን ጉዳት ያጋጠመው አንጋፋው የመሃል ተከላካይ ስቴፋን ዴ ቭሪጅ እና የቶተንሀሙ ዣቪ ሲመንስ ከስብስቡ ውጪ ሆነዋል። የኔዘርላንድ ብሔራዊ ቡድን ወደ ውድድሩ ከማምራቱ በፊት ሰኔ 3 በሮተርዳም ከአልጄሪያ እንዲሁም ሰኔ 8 በኒውዮርክ ከኡዝቤኪስታን ጋር የዓለም ዋንጫ የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎችን የሚያከናውን ይሆናል።
የኔዘርላንዱ ፔድሪ በሚል ስያሜ የተሰጠው ተስፈኛው ኪስ ስሚትም ጥሪው ሳይደርሰው ቀርቷል።
የቡድኑ አምበል ቨርጅል ቫንዳይክ እና የሀገሪቱ የምንጊዜም ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪው ተጫዋች ሜምፊስ ዴፓይ ይህ የዓለም ዋንጫ የመጨረሻቸው እንደሚሆን ይገመታል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ