ግንቦት 04 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ) ከ50.5 ሚሊዮን በላይ መራጮች በሚሳተፉበት 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ፣ የግል ዕጩ ተወዳዳሪዎች የየአካባቢያቸውን ተጨባጭ ችግሮች መሠረት ያደረጉ አማራጭ ሐሳቦችን ይዘው እንደሚቀርቡ ለጣቢያችን ገልጸዋል። በኮልፌ ቀራኒዮ የምርጫ ክልል ዕጩ ተወዳዳሪ ሆነው የቀረቡት የሕግ አማካሪና ጠበቃ አቶ ወንድሙ ኢብሳ፤ ብልሹ አሠራሮችን መቅረፍ የሚቻልበት፣ አገሪቱ የሁሉም ዜጎች መጠለያ የምትሆንበት እና ኢትዮጵያ በየጊዜው ለምትጠይቃቸው ብሔራዊ ጥቅሞች በሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱ እልባት መስጠት የሚያስችሉ ነጥቦችን ያካተተ ባለ 14 ነጥብ ማኒፌስቶ ማቅረባቸውን ገልጸዋል።
በጠቅላላ ምርጫው የግል ዕጩ ተወዳዳሪዎች ጥሩ የሚባል ተሳትፎ እያሳዩ መሆኑን አንስተው፣ የፖለቲካ ሥልጣን በዜጎች ድምፅ ላይ መመሥረት እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
በተመሳሳይ በኦሮሚያ ክልል ኢሉባቦር ዞን የኡካ ምርጫ ክልልን በመወከል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚወዳደሩት ጠበቃና የሕግ አማካሪ አቶ ታደሰ ተክሌ፤ ዕጩ ለመሆን የሚጠይቀው ሂደት በራሱ በፖለቲካ ሥርዓቱ የሐሳብ ልዕልናን ለማምጣትና ጤናማ ፉክክር ለመፍጠር አስተዋጽኦ እንዳለው አብራርተዋል።
ዕጩ ተወዳዳሪዎች ለሕገ-መንግሥቱ የመገዛት እንዲሁም የዜጎችን መብትና ጥቅም የማስከበር ረገድ የራሳቸውን ሚና የመወጣት አቅም እንዳላቸው ገልጸው፤ እርሳቸው በሚወዳደሩበት አካባቢም የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥና አስፈላጊ የመሠረተ-ልማት ዝርጋታዎች እንዲኖሩ ድርሻቸውን እንደሚወጡ አስታውቀዋል። የአካባቢውን ችግር በጥልቀት ማጤን የሚችለው ከሕዝቡ መካከል የሚወጣ ተወዳዳሪ በመሆኑ፣ የግል ዕጩዎች አበክረው መሥራት እንደሚኖርባቸውም አመላክተዋል።
በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ድምፅ ለመስጠት የተመዘገቡ ዜጎች ቁጥር 50 ሚሊዮን 514 ሺህ 155 መሆኑን የምርጫ ቦርድ በቅርቡ ማስታወቁ ይታወሳል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ