ሚያዚያ 12 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ)የሰው ልጅ ገና ያልደረሰባቸው የጥልቅ ባህር ክፍሎች አስደናቂና እንግዳ የሆኑ የሕይወት ዘይቤዎችን ማፍለቃቸውን ቀጥለዋል። በቅርቡ በተደረገ ሳይንሳዊ ፍለጋ የፀሐይ ብርሃን በማይደርስበትና እጅግ አስቸጋሪ በሆነው የውቅያኖስ ጥልቀት ውስጥ፣ የራሳቸውን ብርሃን በማመንጨት በጨለማ ውስጥ የሚበሩ አዳዲስ ዝርያዎች መገኘታቸው ዓለምን አስገርሟል።
እነዚህ ፍጥረታት በሰውነታቸው ውስጥ በሚፈጠር ኬሚካላዊ ሂደት ሙቀት የሌለው ብርሃን የማመንጨት ልዩ ተሰጥኦ ያላቸው ሲሆን፣ ይህ አስደናቂ ክስተት በሳይንሳዊ አጠራሩ “ባዮሉሚነስንስ” (Bioluminescence) በመባል ይታወቃል።
እነዚህ ፍጥረታት የሚያመነጩትን ብርሃን ምግብን ወይም አዳኝን ለመሳብ፣ ጠላትን ለማስፈራራትና ራሳቸውን ለመከላከል እንዲሁም በጭለማ ውስጥ ከሌሎች ተመሳሳይ ፍጥረታት ጋር ግንኙነት ለመፍጠር ይጠቀሙበታል ነው የተባለው።
እስከ 4,000 ሜትር በሚደርስ የውቅያኖስ ጥልቀት ውስጥ የውኃው ግፊት እጅግ ከፍተኛና ቅዝቃዜውም በረዶ እስከመሆን የሚደርስ ቢሆንም፣ ፍጥረታቱ በእነዚህ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ተስማምተው እንዲተርፉ የሚያስችላቸውን አስደናቂ ተፈጥሯዊ ብቃት አዳብረዋል። ይህ ሁኔታ በጥልቁ ዓለም ውስጥ ያለው ብዝሃ ሕይወት ቀደም ሲል ከታሰበው በላይ እጅግ ውስብስብና ሰፊ መሆኑን አመላካች ሆኗል።
ሳይንቲስቶች እንደሚሉት ይህ አዲስ ግኝት የዓለማችን ውቅያኖሶች አሁንም ድረስ በምስጢር የተሞሉና ለሰው ልጅ ጥናት ያልደረሱ መሆናቸውን በድጋሚ ያረጋገጠ ነው። የባህር ውስጥ ፍለጋው በቀጠለ ቁጥር ከዚህ ቀደም ታይተውም ሆነ ተገምተው የማይታወቁ አዳዲስ ዝርያዎች መገኘታቸው አይቀሬ መሆኑ ተጠቁሟል።
ይህም የሰው ልጅ ስለ ምድራችን ውቅያኖሶች ያለው እውቀት ገና ጅምር መሆኑንና በቀጣይ በርካታ ሳይንሳዊ ምስጢሮች እንደሚገለጡ ተስፋ ተጥሎበታል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ