ሚያዝያ 09 ቀን 2018 (መናኸሪያ ሬዲዮ)፦ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከመካከለኛው ምስራቅ ወታደራዊ ውጥረት ጋር በተያያዘ በሰጡት አዲስ መግለጫ፣ ከኢራን ጋር ያለው ጦርነት በታቀደው መሠረት “በጥሩ ሁኔታ” እየተከናወነ መሆኑንና ግጭቱ በቅርቡ ሊያበቃ እንደሚችል ገለጹ። ፕሬዝዳንቱ ዋይት ሃውስ ውስጥ ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ “የምንፈልገውን ማንኛውንም እርምጃ መውሰድ እንችላለን፤ ጦርነቱም በጣም በቅርብ ጊዜ ውስጥ ያበቃል” ሲሉ በራስ መተማመን የታየበት ንግግር አድርገዋል።
ይህ የፕሬዝዳንቱ መግለጫ የወጣው በተለያዩ የኢራን ስልታዊ ወታደራዊ ቦታዎች ላይ የሚሰነዘረው ጥቃት ተጠናክሮ በቀጠለበት ወቅት ነው። ትራምፕ አክለውም የኢራን ወታደራዊ አቅም በተለይም የሚሳኤል እና የባህር ኃይል መሠረተ ልማቶች በከፍተኛ ደረጃ መውደማቸውን ጠቁመዋል። አሜሪካ በአሁኑ ወቅት ያላትን የበላይነት በመጠቀም ኢራን ወደ ድርድር ጠረጴዛ እንድትመጣ ከፍተኛ ጫና እያደረገች መሆኑም ተመላክቷል።
በሌላ በኩል በፓኪስታን አደራዳሪነት የተጀመረው የሁለት ሳምንት የተኩስ አቁም ስምምነት ውይይት እንደቀጠለ ቢሆንም፣ ኢራን ግን ሁሉንም የቀጠናው ግጭቶች ያካተተ ሰፊ ስምምነት ካልተደረገ በስተቀር ድርድሩን እንደማትቀበል እየገለጸች ትገኛለች።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ግን ጦርነቱ ወደ ማብቂያው ምዕራፍ እየተቃረበ መሆኑንና አሜሪካ በቀጠናው ያላትን ግብ በቅርቡ እንደምታሳካ ያላቸውን ጽኑ እምነት ዳግም አረጋግጠዋል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ