ሚያዚያ 06 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ)የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተለያዩ ቋሚ ኮሚቴዎች የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ግምገማ እና የሁለትዮሽ ውይይቶችን ነገ ረቡዕ ሚያዚያ 07 ቀን 2018 ዓ.ም እንደሚያካሂዱ አስታውቀዋል።
ከምክር ቤቱ የኮሙዩኒኬሽን፣ አስተምህሮና ሙዚየም መሪ ሥራ አስፈጻሚ የወጣው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ነገ ከጠዋቱ 2፡30 ጀምሮ ሁለት ዋና ዋና የግምገማ መድረኮች በምክር ቤቱ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ይካሄዳሉ። የሕግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤትን፣ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤትንና የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤትን የዘጠኝ ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት በፊት ለፊት መድረክ የሚገመግም ይሆናል።
በተመሳሳይ ሰዓት፣ የሰው ሀብት ልማት፣ ሥራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የትምህርት ሚኒስቴርን የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት የሚገመግም መሆኑ ተገልጿል። እነዚህ የግምገማ መድረኮች ተቋማቱ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ያከናወኗቸውን ተግባራትና ያጋጠሟቸውን ተግዳሮቶች ለመለየትና ቀጣይ አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ ያለሙ ናቸው።
በሌላ በኩል፣ የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ከናይጄሪያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከመጡ የብሔራዊ ምክር ቤት አገልግሎት ኮሚሽን ልዑካን ጋር የልምድ ልውውጥ ያደርጋል። 13 አባላትን ያካተተው ይህ የናይጄሪያ ልዑካን ቡድን፣ ከቋሚ ኮሚቴው ጋር ነገ ከቀኑ 8፡30 ጀምሮ በምክር ቤቱ በሚኖረው ውይይት በሁለቱ ሀገራት የፓርላማ አገልግሎትና አሠራር ዙሪያ የልምድ ልውውጥ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ