ሚያዚያ 06 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ)አሜሪካ ከኢራን ጋር ያደረገችው ዲፕሎማሲያዊ ንግግር ያለ ስምምነት መጠናቀቁን ተከትሎ፣ በኢራን ወደቦች ላይ ጥብቅ የባህር ላይ እገዳ (Naval Blockade) መጣሏን አስታውቃለች። ይህ እርምጃ በቀጣናው ያለውን ውጥረት ወደ አደገኛ ምዕራፍ ያሸጋገረው ሲሆን፣ የዓለምን የኢነርጂ ገበያ ስጋት ላይ ጥሎታል።
በፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ትእዛዝ የተጀመረው ይህ እገዳ፣ በኢራን ወደቦች በኩል የሚደረጉ ማናቸውንም የንግድ እንቅስቃሴዎች ለማቆም ያለመ ነው። የአሜሪካ ማዕከላዊ እዝ (CENTCOM) እንደገለጸው፣ እገዳው ወደ ኢራን የሚገቡና ከኢራን የሚወጡ መርከቦችን በሙሉ የሚመለከት ነው። ፕሬዝዳንት ትራምፕ በሰጡት መግለጫ፣ እገዳውን ጥሳ ለመሻገር የምትሞክር ማንኛዋም የኢራን መርከብ እርምጃ እንደሚወሰድባትና “ልትጠፋ” እንደምትችል ግልጽ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል። ይሁን እንጂ አሜሪካ እገዳው ወደ ኢራን የማይጓዙ መርከቦች በሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ (Strait of Hormuz) በኩል እንዳያልፉ እንደማይከለክል ገልጻለች።
የአሜሪካን እርምጃ ተከትሎ የዓለም ሁለተኛዋ ግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት ቻይና ጠንከር ያለ ተቃውሞ አሰምታለች። የቻይና ባለስልጣናት ድርጊቱ ዓለም አቀፍ ህግን የጣሰና የሀገራቸውን ብሄራዊ ጥቅም የሚነካ መሆኑን ገልጸዋል። የቻይና መከላከያ ሚኒስትር ዶንግ ጁን በሰጡት መግለጫ፣ ቻይና ከኢራን ጋር ያላትን ህጋዊ የንግድ ግንኙነት እንደምትቀጥልና መርከቦቿም በሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ በኩል ያላቸውን ጉዞ እንደማያቋርጡ አስታውቀዋል።
“ሌሎች ወገኖች በእኛ የንግድ እንቅስቃሴ ላይ ጣልቃ እንዳይገቡ እንመክራለን” በማለት ለዋሽንግተን ቀጥተኛ ማስጠንቀቂያ አስተላልፈዋል። በተጨማሪም የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጉኦ ጂያኩን፣ አሜሪካ በቻይና ላይ የምታቀርበውን “ለኢራን የጦር መሳሪያ ታቀርባለች” የሚል ክስ “መሰረተ ቢስ ስም ማጥፋት” ሲሉ አጣጥለውታል። ቤጂንግ ብቸኛው መፍትሄ የሀይል እርምጃ ሳይሆን ፖለቲካዊ ውይይት መሆኑን ደግማ ገልጻለች።
የኢራን አብዮታዊ ዘብ(IRGC) የአሜሪካን እርምጃ “የባህር ላይ ውንብድና” ሲል የጠራው ሲሆን፣ በሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ ላይ የአፀፋ እርምጃ እንደሚወስድ ዝቷል። ይህ ዛቻ በተለይ በነዳጅ ገበያው ላይ ትልቅ ድንጋጤ የፈጠረ ሲሆን፣ የነዳጅ ዋጋ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሊጨምር እንደሚችል ተገምቷል።
በአሁኑ ወቅት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና የአውሮፓ ህብረት ሁለቱም ወገኖች ራስን የመግታት እርምጃ እንዲወስዱና ወደ ሰላማዊ ድርድር እንዲመለሱ ጥሪ እያቀረቡ ቢሆንም፣ በቀጣናው ያለው ወታደራዊ ዝግጅት ግን ሁኔታው ወደ ከፋ ግጭት ሊያመራ እንደሚችል አመላካች ሆኗል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ