በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የወጣው ባንኮች እስከ ምሽት 3:30 ሰዓት ድረስ አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያስገድደው መመሪያ ከባንኮች አሠራር ጋር የማይጣጣም መሆኑን ማህበሩ ለመናኸሪያ ሬዲዮ ገልጿል፡፡
ባንኮች በዘመናዊ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም አማካይነት የተለያዩ የባንክ አገልግሎቶችን ለደንበኞቻቸው በቀላሉ ማቅረብ እየቻሉ በመሆኑ፣ የምሽት አገልግሎት አላስፈላጊና አግባብነት የሌለው መሆኑን የባንኮች ማህበር አስታዉቋል።
የባንኮች ማህበር ዋና ጸሀፊ አቶ ደምሰው ሞገስ እንደሚገልጹት፣ደንበኞች በፖስ ወይም ኤቴኤም ማሽኖች፣ በተንቀሳቃሽ ስልክ የባንክ መትግበሪያዎችና በኢንተርኔት ባንኪንግ አማካይነት የሚፈልጉትን አገልግሎት ማግኘት ስለሚችሉ ባንኮች እስከ ምሽት ክፍት ሆነው መቆየት አለባቸዉ የሚለዉ አስገዳጅ መመሪያ ተገቢ አይደለም ብለዋል፡፡
በተጨማሪም ማህበሩ በፌዴራል መንግሥት ሥር ያሉ ተቋማትን የከተማ አስተዳደር በመመሪያ እንዲያስተዳድር የተሰጠው ሥልጣን አግባብ እንዳልሆነና ይህ መመሪያ ከመውጣቱ በፊት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስተያየት መጠየቅ እንደነበረበት ይገልጻሉ።
በተለይም ይህ መመሪያ የባንኮችን የስራ ባህሪ ያላገናዘበና ለባንኮችም ሆነ ለደንበኞች ደህንነት አስጊ ሊሆን የሚችል መሆኑን የገለጹት ዋና ጸሃፊው አቶ ደምሰው በምሽት የሚሰጥ የባንክ አገልግሎት ለዘረፋና ለሌሎች የደህንነት ስጋቶች ሊያጋልጥ እንደሚችል ተናግረዋል ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ደምብ 185/2017 የተሰኘ የትራንስፖርት አገልግሎቱን ምሽት 4 ሰዓት ድረስ በመንገድ ዳር የሚገኙ የንግድ እና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ደግሞ ምሽት 3:30 ሰዓት ድረስ እንዲቆዩ የሚያስገድድ ደምብ ከየካቲት 29 ጀምሮ ተግባራዊ ማድረጉ ይታወሳል።
ምላሽ ይስጡ