ሰኔ 11 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ) በተያዘው የሰኔ ወርና በመጪዎቹ ጊዜያት በርካታ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎቻቸውን የሚያስመርቁ መሆኑን ተከትሎ፣ መናኸሪያ ሬዲዮ ከሥራ ዕድል ፈጠራ ጋር በተያያዘ ተቋማቱን አነጋግሯል።
በጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ፣ ምርምር፣ ቴክኖሎጂ ሽግግርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፖል ቦት፤ በተቋሙ ትምህርታቸውን አጠናቀው የሚመረቁ ተማሪዎች በቀጥታ ሥራ እንዲያገኙ ትስስር መፈጠሩን ተናግረዋል፡፡
በወርቅ ማውጣት ሥራ ላይ ከተሰማሩ ድርጅቶች፣ ከባንኮችና ከኢንዱስትሪዎች ጋር ጨምሮ በጥቅሉ ከ11 ከሚሆኑ ተቋማት ጋር ትስስር መፈጠሩን ገልጸው፤ በተለይም በትምህርታቸው ላይ ከፍተኛ ውጤትና ጥሩ አቅም ያላቸው ተማሪዎች ቅድሚያ ዕድል እንዲያገኙ ከድርጅቶቹ ጋር ስምምነት ላይ መደረሱን አስረድተዋል፡፡
ምክትል ፕሬዚዳንቱ አክለውም፣ ተማሪዎቹ ከመመረቃቸው በፊት በሥራ ፈጠራና በሥራ ዕድል ፍለጋ ቴክኒኮች ላይ ሥልጠናዎች እንደተሰጧቸው ገልጸዋል፡፡ ሆኖም እንደ አንትሮፖሎጂና ሳይኮሎጂ ባሉ የትምህርት መስኮች ለሚመረቁ ተማሪዎች ከቢዝነስ ተቋማት ጋር ትስስር ለመፍጠር ተግዳሮት እንደሆነባቸው አንስተዋል።
በተመሳሳይ ሁኔታ በጉዳዩ ላይ ጣቢያችን ያነጋገራቸው በእንጂባራ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ፕሮግራም ዳይሬክተር ዶ/ር ሀብታሙ ዘገየ፤ በተቋሙ ለዚሁ ጉዳይ የሚሆን በጀት ተይዞ በሥራ ፈጠራ ላይ ሰፊ ሥልጠና ሲሰጥ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡
ተማሪዎች ከተመረቁ በኋላ ሊገጥማቸው ስለሚችለው አዲስ የሕይወት መንገድ የሥነ-ልቦና ዝግጅት እንዲኖራቸው ሲሠራ መቆየቱንም አስታውቀዋል።
በተለይም ተመራቂ ተማሪዎች በኢንተርንሺፕ (በተግባር ልምምድ) በሠሩባቸው ተቋማት ውስጥ በቋሚነት እንዲቀጠሩ ከማድረግ አንጻር ጅምር ሥራዎች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡
ተማሪዎቹ ተመርቀው ከወጡ በኋላ ምን ያህሉ ሥራ አገኙ በሚለው ጉዳይ ላይም ተቋማቱ ክትትልና ድጋፍ እንደሚያደርጉ አብራርተዋል ።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ