ሐምሌ 30 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ) በምእራብ ጎጃም ዞን በፍኖተ ሰላም ከተማ አስተዳደር ለመንግስት ስራ የተሰጠዉን ላፕቶፕ ለግል ጥቅሙ ለማዋል በማሰብ የማጭበርበር ወንጀል የፈጸመው ተከሳሽ በጽኑ እስራት ተቀጥቷል።
በከተማ አስተዳደሩ መስከረም 23 አና 24 ቀን 2017 ዓ. ም በመንግስት ተቋማት ላይ የተፈጸመውን ዝርፊያ ተከትሎ የመንግስት ሰራተኞች በትክክል የተዘረፈባቸውን የስራ ቁሳቁሶች ለንብረት ክፍል ሪፖርት እንዲያደርጉ መደረጉ ይታወሳል።
ተከሳሽ ጌትነት ከበደ በፍኖተ ሰላም ከተማ አስተዳደደር የስነ ምግባር መኮንን ሙያተኛ ሲሆን ለመንግስት ስራ እንዲገለገልበት የተሰጠዉን ላፕቶፕ ለግል ጥቅሙ ለማዋል በማሰብ “ተዘርፎብኛል” የሚል የሀሰት ሪፖርት ለመንግስት አቅርቧል።
ይሁን እንጅ የከተማ አስተዳደሩ ፖሊስ ጽ/ቤት ከህብረተሰቡ በደረሰው ጥቆማ ጥር 23 ቀን 2017 ዓ ም በመኖሪያ ቤቱ ድንገተኛ ፍተሻ አድርጓል። በዚህም ተከሳሽ ቤት ውስጥ በጸጥታ ችግሩ ምክንያት “ተዘርፌአለሁ” በሚል ሪፖርት የተደረገው ላፕቶፕ ከቤቱ ውስጥ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሏል።
ከዚህ በተጨማሪም በህግ እንዲያዝ ከተፈቀደለት ጥይት ውጭ 60 ፍሬ የክላሽ ጥይት በቁጥጥር ስር መዋሉ ተገልጿል።
የከተማ አስተዳደሩ ፖሊስም በተጠርጣሪዉ ላይ የወንጀል ምርመራ አጣርቶ ለምዕራብ ጎጃም ዞን ፍትህ መምሪያ ክስ እንዲመሰረትበት አቅርቧል፡፡
የምዕራብ ጎጃም ዞን ፍትህ መምሪያ ዐቃቢ ህግም የቀረበዉን የምርመራ መዝገብ ተመልክቶ ተከሳሽ ወንጀል ስለመፈጸሙ በበቂ ማስረጃ የተደገፈ ሆኖ ስላገኘዉ በከባድ ማታለል የሙስና ወንጀል እና ህግ ወጥ የጦር መሳሪያ መያዝ ወንጀል ክስ መስርቶበታል፡፡
ክሱ የቀረበለት የምዕራብ ጎጃም ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤትም ግራ ቀኙን አከራክሮ ተከሳሽ የቀረበበት ክስ ክዶ የተከራከረ ቢሆንም በዐቃቢ ህግ የቀረበበትን ማስረጃ ማስተባበል ባለመቻሉ በተከሰሰበት ክስ ጥፋተኛ በማለት የግራ ቀኙን የቅጣት አስተያየት ግምት ዉስጥ በማስገባት ጥፋተኛ መሆኑን አረጋግጧል።
ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ሃምሌ 29/2017 ዓ.ም በዋለው ችሎት ለተከሳሽ እና መሰል አጥፊዎች ያስተምራል በሚል በ7 ዓመት ከ8 ወር ጽኑ እስራት እና በ2 ሺ ብር እንዲቀጣ መወሰኑን መናኸሪያ ሬዲዮ ከምዕራብ ጎጃም ዞን ኮሙኒኬሽን ሰምቷል::
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ 👉 https://t.me/menaharia_fm
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን 📞
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63
ምላሽ ይስጡ