ቤተሰብን በመደገፍ ስራ ውስጥ የመዋቅርና የፖሊሲ ማዕቀፍ ችግር መኖሩን ለጣቢያችን የገለጸው የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ነው።
ኢትዮጵያ አለም አቀፍ የቤተሰብ ህጎችን የተቀበለች ሀገር ብትሆንም ቤተሰብን በአግባቡ አደራጅቶ ከመደገፍ አንጻር በቂ ፖሊሲና መርህ አለመኖሩን በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የማህበራዊ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ሁሪያ ዓሊ አስታውቀዋል።
አሁን ላይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለቤተሰብ ጉዳይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታዋ ነገር ግን እስከ ታች ወርዶ ለመስራት የመዋቅርም ሆነ የፖሊሲ ችግር መኖሩን ነው የጠቀሱት።
በመሆኑም የቤተሰብ ጉዳይ ትኩረት እንዲሰጠው የህግ ማዕቀፍ እና መዋቅር ተስተካክሎ እንዲተገበር እየተሰራ መሆኑን ወ/ሮ ሁሪያ ተናግረዋል።
ሚኒስቴሩ ቤተሰብን ለማገዝ በማህበራት በኩል እየሰራ ቢሆንም፤ በገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ የተቋሙ በጀት በቂ አለመሆኑን ነው ሚኒስትር ዴኤታዋ የገለጹት።
ይሁን እንጂ የሀገርን ባህልና እሴት ለማስቀጠል ቤተሰብ ላይ መስራት ተገቢ ነው በሚል እንደ አዲስ ትኩረት የተሰጠው በመሆኑ አጋዥ አካላትን በስፋት የማስተባበር ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ቤተሰብ ላይ ለመስራት መዋቅርና ፖሊሲዎች የግድ አስፈላጊ ናቸው የሚሉት ወ/ሮ ሁሪያ የዘንድሮው የቤተሰብ ቀን የፊታችን ሐሙስ ግንቦት 7 ቀን 2017 ዓ.ም የተሻሻለ የቤተሰብ ስራና ገቢ ለሀገር ኢኮኖሚ በሚል መሪ ቃል እንደሚከበር አስታውቀዋል።
ምላሽ ይስጡ