ታኅሳስ 04 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ) ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በቱርክ አደራዳሪነት ያደረጉት ስምምነት አፈፃፀሙ ውጤታማ እንዲሆን በጥንቃቄ መያዝ እና መመራት እንዳለበት የገለጹት የአለም አቀፍ ግንኙነት እና የፖለቲካ ተንታኞች ናቸው፡፡
የአለም አቀፍ ግንኙነት መምህሩ አቶ እያሱ ሃይለሚካኤል፤ እንደዚህ አይነት ስምምነቶች አለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ሂደቶችን መሰረት ያደረጉና ሂደቱን ለማጠናከርም ከባድ የቤት ስራን የሚጠይቅ ነው ብለዋል፡፡
በአጭር ጊዜ ሳይሆን በሂደት ለውጦችን ሊያመጣ ይችላል ያሉት ባለሙያው፤ በተለይም የሁለትዮሽ ቀጠናዊ አሰላለፍ እና በሃገራት መካከል የሚኖረውን ኢኮኖሚያዊ፤ ዲፕሎማሲያዊ እንዲሁም ወታደራዊ ጉዳዮችን የሚቀይር በመሆኑ ከፍተኛ ጥንቃቄን የሚፈልግ ነው ብለዋል፡፡
የቴክኒክ ጉዳዮችን የሚፈጽሙ ባለሙያዎች ሰነዶችን በማርቀቅ ሒደት የሃገርን ብሔራዊ ጥቅም ማስቀደም እንደሚገባቸው አመላክተዋል።
የፖለቲካ ተንታኝ እና የስነ አመራር ባለሙያው አቶ ጌትዬ ትርፌ በበኩላቸው በሁለቱ ሃገራት መካከል የተደረገው ስምምነት ዝርዝር ሰነዱ ግልፅ ባይደረግም የሁለትዮሽ ፍቃደኝነትን መሰረት ያደረገ በመሆኑ መልካም ነው ብለዋል፡፡
ተፈጻሚነቱ ውጤታማ እንዲሆን በአለም አቀፍ ህግጋት የተመራ የሃገራችንን ሉዓላዊነት እና ጥቅም የሚያስጠብቅ መሆን ይገባዋልም ነው ያሉት፡፡
የኢትዮጵያን ዘላቂ የባህር በር አማራጭ ባለቤትነትን ያረጋገጠ መሆን እንደሚኖርበት የተናገሩት ባለሙያው፤ የሁለቱንም አገራት ተጠቃሚነት በማረጋገጥ የሰጥቶ መቀበል መርህን መሰረት ያደረገ ብሎም ሉአላዊነትን ያስጠበቀ እንዲሆን በጥንቃቄ የተሞላ አካሄድ ያስፈልገዋል ሲሉ አመላክተዋል።
ሁለቱ ጎረቤት አገራት ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ የገቡበትን ውጥረት የሚፈታ ስምምነት በቱርክ አንካራ ማድረጋቸው ይታወቃል፡፡
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
መናኸሪያ ሬዲዮ 99.1
ሃሳብ፣አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት የሚከተሉትን የስቱዲዮ ስልኮቻችን ይጠቀሙ
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63
የቀጥታ ስርጭት 👉 📻 (https://worldradiomap.com/et/play/menaharia) radio 99.1 (https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
✅ Telegram (https://t.me/menaharia_fm)
ትክክለኛውን የመናኸሪያ ሬዲዮ የዩቱዩብ አድራሻ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
➲ Youtube (https://www.youtube.com/channel/UC8uROsU69D8Ob65XapeHvIw)
ምላሽ ይስጡ