ኅዳር 19 ቀን 2019(መናኸሪያ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ የደምና ቲሹ ባንክ አገልግሎት (EBTBS) ከዓለም አቀፉ የጤና ተቋም አቦት (Abbott) ጋር በመተባበር፣ አዲሱን ትውልድ በበጎ ፈቃደኝነት ደም እንዲለግስ ለማነሳሳትና በሀገሪቱ ያለውን የደም እጥረት ለመቅረፍ ያለመ “The Human Chain” የተሰኘ ሀገር አቀፍ የግንዛቤ ማስጨበጫ ዘመቻ ዛሬ በይፋ አስጀምረዋል።
ዘመቻው በወሊድ ወቅት ደም የሚያስፈልጋቸውን እናቶች፣ የድንገተኛ ቀዶ ጥገና ታካሚዎችንና አስቸኳይ ደም የሚሹ ህሙማንን ሕይወት ለመታደግ ያለመ ነው።

የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) መስፈርት የአንድ ሀገር መሠረታዊ የደም ፍላጎት እንዲሟላ ከህዝቡ ቢያንስ 1 በመቶው ደም መለገስ እንዳለበት ቢያስቀምጥም፣ ኢትዮጵያ በዓመት ከሚያስፈልጋት 1.1 ሚሊዮን ዩኒት ደም ውስጥ እየሰበሰበች ያለችው 476,000 ዩኒት ገደማ (43.1 በመቶውን) ብቻ መሆኑ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ደምና ቲሹ ባንክ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አሸናፊ ታዘበው በመድረኩ ላይ እንደተናገሩት፣ መስፈርቱን የሚያሟላ እያንዳንዱ ወጣት በዓመት ሦስት ጊዜ ደም ቢለግስ አሁን ያለውን የደም አቅርቦት ክፍተት ሙሉ በሙሉ መሙላት ይቻላል።
በመሆኑም ህብረተሰቡ በተለይም ወጣቶች ኅዳር 26 ቀን (ዲሴምበር 5) በአቅራቢያቸው ወደሚገኝ የደም ልገሳ ጣቢያ በመሄድ ደም እንዲለግሱ ጥሪ አቅርበዋል።

የአቦት የደም ዝውውር ዘርፍ (MEAP & Russia/CIS) ማኔጂንግ ዳይሬክተር ኦትባህ ጋድባን በበኩላቸው፣ ወጣቶች በማኅበረሰባቸው ውስጥ ዘላቂ ለውጥ የማምጣት ትልቅ አቅም እንዳላቸው ጠቅሰው፣ አዲሱን ትውልድ ለማስተማርና ለማብቃት ከአገልግሎቱ ጋር በአጋርነት በመሥራታቸው ኩራት እንደሚሰማቸው ገልጸዋል።
የመጀመሪያው የደም ልገሳ መርሐ-ግብር ዛሬ ቅዳሜ ኅዳር 19 ቀን 2019 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ዋና መሥሪያ ቤት ፊት ለፊት በሚገኘው የመነሻ ምድር (Land of Origin) ሕንፃ የሚካሄድ ሲሆን፣ በቀጣዮቹ ሦስት ወራት ውስጥ በመላ ሀገሪቱ ተጠናክሮ ይቀጥላል።
ህብረተሰቡ ስለ ደም ልገሳ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በነፃ የስልክ መስመር 8040 መደወል ወይም በአቅራቢያው ወደሚገኝ የደም ባንክ ጣቢያ መሄድ እንደሚችል ተመልክቷል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ