ሕዳር 11 ቀን 2019(መናኸሪያ ሬዲዮ)በሽታው በአብዛኛው ከአምስት ዓመት በታች ባሉ ህጻናት ላይ እንደሚከሰት ዛሬ እየተከበረ በሚገኘው ዓለም አቀፍ የሳንባ ምች ቀን መድረክ ላይ ተገልጿል።
በዓለም ለ18ኛ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ7ኛ ጊዜ “ሳንባ ምችን የመቆጣጠር አዲስ ምዕራፍ” በሚል መሪ ቃል እየተከበረ የሚገኘው የዘንድሮው የሳንባ ምች ቀን፣ እስከ 14 ዓመት ዕድሜ ያሉ ህጻናትን ለማካተት ያቀደ ስለመሆኑም በጤና ሚኒስቴር የአፍላ ወጣቶች የጤና አጠባበቅ መሪ ሥራ አስፈጻሚ ሲስተር ዘምዘም መሃመድ ተናግረዋል።
የሳንባ ምች በብዛት ከአምስት ዓመት በታች ባሉ ህጻናት ላይ የሚከሰትና በአግባቡ መቆጣጠርና መከላከል ካልተቻለ ገዳይ በሽታ መሆኑንም መሪ ሥራ አስፈጻሚዋ ገልጸዋል። በዓለም አቀፍ ደረጃ በሳንባ ምች ምክንያት ከ45 ሺህ በላይ ህጻናት እንደሚሞቱም አክለዋል። በሽታው ህጻናትን ለሞት ከሚዳርጉ በሽታዎች መካከል 18 በመቶ ያህል ድርሻ እንደሚይዝም ሲስተር ዘምዘም አስረድተዋል።
በኢትዮጵያም በሽታው ከፍተኛ ትኩረት እንደሚያስፈልገው የጠቀሱት መሪ ሥራ አስፈጻሚዋ፣ የጤና ባለሙያዎች፣ ወላጆችና የህክምና ተቋማት ቁርጠኝነት ሊያድግ እንደሚገባም ተናግረዋል። ሚኒስቴሩ “አዲስ ምዕራፍ” በሚል ከአምስት ዓመት በላይ ባሉ ልጆች ላይ ትኩረት ለማድረግ ከያዝነው ዓመት ጀምሮ ማቀዱንም ብለዋል።
ከአምስት ዓመት በታች ላሉ ህጻናት ዘርፍ በጥቅሉ ለህክምና የሚያገለግሉ የቁሳቁስና የግብዓት እጥረት መኖሩም በመድረኩ ተገልጿል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ