ሕዳር 05 ቀን 2019(መናኸሪያ ሬዲዮ) መቀመጫውን በዱባይ ያደረገው የቴክኖሎጂ ኩባንያ ያንጎ ግሩፕ፣ በመላው አፍሪካ እየተገበረ ያለውን “ደኅንነቱ የተጠበቀ የትምህርት ቤት ጉዞ” (Safer Journeys to School) የተሰኘውን ተነሣሽነት ወደ ኢትዮጵያ በማስፋፋት ከ12,500 በላይ ለሆኑ ተማሪዎች የመንገድ ደኅንነት ሥልጠና መስጠቱ ተገለጸ።

ኅዳር 5 ቀን 2019 ዓ.ም በአዲስ አበባ በይፋ የተጀመረው ይህ መርሐ ግብር፣ ከሴቭ ዘ ኔሽን (STN) እና ከአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለሥልጣን ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ነው።
ፕሮግራሙ በመዲናዋ በሚገኙ አራት ትምህርት ቤቶች ለ25 ቀናት የቆየ ተግባራዊ የመንገድ ደኅንነት ትምህርት ከመስጠቱ ባሻገር፣ በሁለቱ ትምህርት ቤቶች አካባቢ የእግረኞች መሻገሪያ፣ የፍጥነት መቀነሻ ጉብታዎች፣ የትራፊክ ምልክቶችና መከላከያ አጥሮችን የማሻሻል ሥራ አከናውኗል።
በመርሐ ግብሩ ማስጀመሪያ ላይ የተገኙ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ተነሣሽነቱ መንግሥት ከያዘው የመንገድ ደኅንነት ስትራቴጂ ጋር የሚጣጣም መሆኑን ጠቅሰው፣ ለሌሎች ትምህርት ቤቶችም ጠቃሚ ተሞክሮ የሚሆን ሞዴል መፍጠሩን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የያንጎ ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር የቀናለም አበበ በበኩላቸው፣ ተቋማቸው ከቴክኖሎጂ አገልግሎት ባለፈ ለማኅበረሰቡ የዕለት ተዕለት ደኅንነት ትኩረት እንደሚሰጥና ሕጻናት ወደ ትምህርት ቤት ሲጓዙ በራስ መተማመን እንዲኖራቸው እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት ሪፖርትን ዋቢ በማድረግ በኢትዮጵያ በየዓመቱ ከ21 ሺህ በላይ ሰዎች በመንገድ አደጋ ሕይወታቸውን እንደሚያጡ የገለጹት በኢትዮጵያ የሴቭ ዘ ኔሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ ምስጋናው ቢምረው፣ መርሐ ግብሩ በትምህርት ቤቶች የደኅንነት ኮሚቴዎችና ክበባት አማካኝነት ዘላቂነት እንዲኖረው መደረጉን አስረድተዋል።

ከዚህ ቀደም በዛምቢያና በሴኔጋል ከ34 ሺህ በላይ ሕጻናትን ተጠቃሚ ያደረገው ይህ ፕሮግራም፣ ያንጎ ግሩፕ በኢትዮጵያ ከሚያከናውናቸው እንደ የደም ልገሳ፣ “Yango Cares” እና የወጣቶች የSTEM ፌሎውሺፕ ፕሮግራም ካሉ ማኅበረሰብ ተኮር ተግባራት መካከል አንዱ መሆኑ ተገልጿል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
© 2026 Menahria f.m 99.1. All rights reserved.
ምላሽ ይስጡ