ከ1 ሺህ በላይ ልዑካንን የሚያሳትፈውን የ2027 የአፍሪካ ንግድ ጥምረት ጉባኤ (ኤሲሲኤስ 2027) ኢትዮጵያ እንድታስተናግድ የሚያስችል የአጋርነት ስምምነት ትናንት ዓርብ በአዲስ አበባ ተፈረመ።
ስምምነቱን የጉባኤው ጠንሳሽ ናይጄል ኮሊን ታተርሳል፣ የኢትዮጵያ ማርኬቲንግ ባለሙያዎች ማህበር (ኢኤምፒኤ) ፕሬዝዳንት ፋና አ. አባይ እና የኢትዮጵያ የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ማህበር (አይሲቲ-ኢቲ) ፕሬዝዳንት ይልቃል አባተ ተፈራርመውታል።

ጉባኤው በማርኬቲንግ፣ በቴክኖሎጂ፣ በአቅርቦት ሰንሰለትና ሎጂስቲክስ እንዲሁም በፈጠራ ኢኮኖሚ ዘርፎች የተሰማሩ የአፍሪካ የንግድ መሪዎችን፣ ፖሊሲ አውጪዎችንና ባለሙያዎችን በአንድ መድረክ እንደሚያገናኝ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ማርኬቲንግ ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዝዳንት ፋና አ. አባይ ጉባኤው የሀገር ውስጥ ኩባንያዎችን ከአፍሪካ ገበያ ጋር በማስተሳሰር አዲስ አበባን የአህጉሪቱ የንግድ መገናኛ ማዕከል ለማድረግ ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥር ገልጸዋል።
የጉባኤው ጠንሳሽ ናይጄል ኮሊን ታተርሳል በበኩላቸው፣ በዛምቢያ የተጀመረውን የአፍሪካ ንግድ ትብብር በኢትዮጵያ ይበልጥ ለማስፋት መታቀዱን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያውን ጉባኤ ዝግጅት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክ ባለሙያዎች ማህበር እና የኢትዮጵያ የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ማህበር ከኢትዮጵያ ሎጂስቲክስ እና የአቅርቦት ሰንሰለት አስተዳደር ባለሙያዎች ማህበር (ኢኤልኤስኤ) እንዲሁም ከተለያዩ አህጉራዊ ኮንፌዴሬሽኖች ጋር በመተባበር በጋራ ይመሩታል።
ጉባኤው ከአንድ ጊዜ ስብሰባ ባለፈ ዘላቂ የንግድና የሙያ ትብብርን ለመፍጠር ያለመ ሲሆን፣ ዝርዝር መርሐ-ግብሮቹ በቀጣይ እንደሚፋ ‑የሚደረጉ መሆኑ ተገልጿል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ