ጥቅምት 24 ቀን 2019(መናኸሪያ ሬዲዮ) አንቲጓዋ እና ባርቡዳ ሴንት ጆንስ ከተማ በተካሄደው የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ የአይን ጤና ጉባኤ ላይ የተሳተፈችው ኢትዮጵያ፤ እስከ እ.ኤ.አ. 2030 ድረስ 41 ሚሊዮን ዜጎችን የአይን ጤና አገልግሎት ተጠቃሚ የሚያደርግ የሁለት ሚሊዮን ዶላር እቅድ ይፋ አደረገች።

ጉባኤው በአንቲጉዋ እና ባርቡዳ፣ ባንግላዲሽ፣ ጉያና፣ አየርላንድ እና ናይጄሪያ መንግስታት አዘጋጅነት ከዓለም ጤና ድርጅት እና ከዓለም አቀፉ የዓይን ዓይነ ስውርነት መከላከል ኤጀንሲ ጋር በመተባበር የተካሄደ ነው። በዚሁ መድረክ ኢትዮጵያ የመጀመሪያ ደረጃ የአይን ጤና አገልግሎትን ከሀገሪቱ ሁለንተናዊ የጤና ሽፋን ጋር በማቀናጀት ላከናወነችው ሥራ «Global Vision Impact Award» የተሰኘ ሽልማት ተበርክቶላታል።
በጤና ሚኒስቴር የጤና አገልግሎትና ፕሮግራሞች ዘርፍ ሀገራዊ የህክምና ዘመቻዎች አስተባባሪ እና የሚኒስትር ዴኤታ ከፍተኛ አማካሪ ዶክተር ሌሊሳ አማኑኤል በተገኙበት ይፋ በተደረገው በዚህ እቅድ፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ3,200 በሚበልጡ የመጀመሪያ ደረጃ የጤና ተቋማት ውስጥ ጥራት ያለው የአይን ህክምናን ማጠናከር፣ የመነጽር አቅርቦትን ማስፋፋት፣ የቅድመ-ምርመራ እና የሪፈራል ስርዓትን ማሻሻል እንዲሁም የዓይን ሞራ ህመም ቀዶ ህክምና ጥራትና ውጤትን ማሳደግ ታቅዷል።

ይህ ኢንቨስትመንት ከእ.ኤ.አ 2030 በፊት 50 በመቶ የሚሆኑ የትምህርት ቤት ተማሪዎችን የአይን ጤና ሽፋን ውስጥ ለማካተት ለተያዘው ሀገራዊ ግብ ትልቅ ድጋፍ እንደሚሆን ተመላክቷል።
ዶክተር ሌሊሳ አማኑኤል በጉባኤው ላይ ባስተላለፉት መልእክት ማንኛውም የኢትዮጵያ ዜጋ በእድሜ፣ በፆታ፣ በገቢ፣ በዓይን ሞራ ህመም ወይም በመኖሪያ ቦታ ሳይወሰን ጥራት ያለውና ተደራሽ የሆነ የአይን ህክምና እንዲያገኝ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በህብረት በመስራት መከላከል የሚቻልን የእይታ ማጣት መቅረፍ እና እይታን መመለስ እንደሚቻል ጠቁመው፣ ይህም ሁሉንም ዜጋ ተጠቃሚ የሚያደርግ የጤና ስርዓት እውን ለማድረግ እንደሚረዳ አብራርተዋል።
በጉባኤው ላይ ይፋ እንደተደረገው «Vision Action Fund» የተሰኘው ዓለም አቀፍ ድርጅት ለኢትዮጵያን ጨምሮ ለ24 አገራት የ10 ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያደርግ የገለጸ ሲሆን፣ እንደ «ኦርቢስ ኢንተርናሽናል» ያሉ ተቋማትም ከ2027 እስከ 2030 ባለው ጊዜ ውስጥ የሚውል የ32 ሚሊዮን ዶላር የገንዘብና ቴክኒካዊ ድጋፍ ይፋ አድርገዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ1.1 ቢሊዮን በላይ ሰዎች በቅድመ መከላከል ወይም በሕክምና ሊድኑ የሚችሉ የእይታ ማጣት ችግር እንደሚገጥሟቸው በጉባኤው ላይ መገለጹ ይታወሳል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን

ምላሽ ይስጡ