
ጥቅምት 11 ቀን 2019(መናኸሪያ ሬዲዮ)በዳንጎቴ ፕሮጀክት ላይ ኢትዮጵያውያን 10 በመቶ የኢንቨስትመንት ድርሻ እንዲኖራቸው መገለፁ ይታወሳል።
ኢትዮጵያውያን በትላልቅ የኢንዱስትሪ ፕሮጀክቶች ውስጥ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ማስቻል ድርሻ እንዲኖራቸው ከማድረግ ባለፈ በውጪ ሀገራት ፕሮጀክቶች ላይ የመሳተፍ እድልን ይፈጥራል ሲሉ የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ለጣቢያችን ገልፀዋል።
ኢንቨስትመንቱ በግልጽነትና በተገቢው የፋይናንስ አስተዳደር ከተመራ ባለሃብቶች ከፕሮጀክቱ ትርፍ የሚያገኙበት፣ ካፒታላቸውን የሚያሳድጉበት እና የሌሎች ውጭ ሀገራት ድርሻዎችን በመግዛት ተሳታፊ የሚሆኑበትን ዕድል ይፈጥራል ሲሉ የሚገልፁት የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በረኸተስፋ ናቸው።
ከዚህ ቀደም በትላልቅ ፕሮጀክቶች በአውሮፓ ሀገራት ብቻ የሚገዛ ቢሆንም፣ የዳንጎቴ ፕሮጀክት በአፍሪካውያን ብቻ እንዲያዝ መወሰኑ እና ኢትዮጵያውያንንም ተሳታፊ ማድረጉ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ትልቅ አስተውሎት እንደሚኖረው አብራርተዋል።
ይህንኑ ሃሳብ የሚያጠናክሩት ሌለኛው የምጣኔ ሃብት ባለሙያ ዶክተር ጉቱ ቴሶ ፕሮጀክቱ ኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኙ ግብዓቶች የሚከናወን በመሆኑ ኢትዮጵያውያን ባለሃብቶችን ተሳታፊ ማድረጉ ተገቢነት ያለው ነው ብለዋል። ሙሉ ለሙሉ ሀብቱ ከኢትዮጵያ የሚወጣበትን እድል በመቀነስ በሀገሪቱ ውስጥ ያሉ ባለሃብቶችንም ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችል ነው ሲሉ ገልፀዋል።
ይህንን ግዙፍ ፕሮጀክት ተከትሎ በሌሎች ዘርፎች ላይ ኢንቨስት የሚያደርጉ አካላትን የሚስብ በመሆኑ እንደ ሀገር ያለው ፋይዳ ከፍተኛ ነው ብለዋል።
አሊኮ ዳንጎቴ በኢትዮጵያ በወርቅ፣ በማዳበሪያ እና በነዳጅ ዘርፎች ላይ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን በመገንባት ሂደት ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ