ጥቅምት 09 ቀን 2019 (መናኸሪያ ሬዲዮ) ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ የባህር በር ባለቤት እንደነበረች በመግለጽ፣ የታሪክ፣ የተፈጥሮ እንዲሁም የጂኦ-ፖለቲካ መብቶቿን በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ ማስጠበቅ እንደሚገባ ያስታወቀው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ነው።
በታሪክ አጋጣሚ ያጣነውን የባህር በር ለማስመለስ ህዝቡ ነቅቶ ሊጠይቅና የህዳሴ ግድቡ እንደተሳካው ሁሉ ይህንንም መብት ማሳካት እንደሚያስፈልግ ተገልጿል።
ምሁራንን፣ ወጣቶችን እና ማህበረሰቡን በማሳተፍ ታሪካዊ፣ ተፈጥሯዊ እና ጂኦ-ፖለቲካዊ እውነታውን ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ በማስረዳት ኢትዮጵያ ያጣችውን መብት በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ መልሶ ማግኘት የምትችልበትን አማራጭ መፈጠር እንደሚገባ የገለጹት የጽሕፈት ቤቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አረጋዊ በርሄ ናቸው።
ኢትዮጵያ ከጥንቱ የአዶሊስ ዘመን ጀምሮ የባህር በር እንደነበራት፣ ከምንም በላይ እንደ ግራር፣ ዘይላ፣ ኸርጊጎ የመሳሰሉ የባህር በሮች በተለያዩ መንግስታት ስር እንደነበሩ በማስታወስ፤ ከህዳሴ ግድብ ስኬት ጋር በማያያዝ የውሃ ማስተዳደር አቅምን ማጠናከር እንደሚገባ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ለግብጽ ያበረከተችው ውሃ ብቻ ሳይሆን ለም አፈር ጭምር እንደሆነ ያስታወቁት ዶክተር አረጋዊ፤ ሀብቱን በአግባቡ በመጠቀም ረገድ ክፍተቶች እንደነበሩና የሌሎች ሀገራት ጫናዎች መኖር ኢትዮጵያ እንዳትረጋጋ አልፎ ተርፎም ፍላጎቶቿን ማሟላት እንዳትችል ተግዳሮት መፍጠሩን ጠቅሰዋል።
የታሪክ፣ የህግ እና ጂኦ-ፖለቲካዊ መብቶችን መሰረት በማድረግ፣ ህብረተሰቡ በሰላማዊ መንገድ ጥያቄውን እንዲያነሳ ማድረግ እና ትውልዱ የ”ይቻላል” መንፈስን ይዞ እንዲቀጥል ማስተማር እንደሚገባ ዋና ዳይሬክተሩ አመላክተዋል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ