መስከረም 26 ቀን 2019(መናኸሪያ ሬዲዮ)በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ከወሊድ በኋላ የሚከሰት የደም መፍሰስን (PPH) ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ያለመ መርሃ ግብር «Strengthening Prevention, Preparedness, and Response to Postpartum Hemorrhage: Saving Mothers’ Lives Through Timely and Quality Care» በሚል መሪ ቃል ተካሄዷል።
መርሐ ግብሩን በጋራ ያዘጋጁት የኢትዮጵያ የጽንስና የማህፀን ሐኪሞች ማህበር (ESOG)፣ የፌደራል ጤና ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ አዋላጅ ነርሶች ማኅበር እና የዓለም አቀፍ የማኅፀንና ፅንስ ሐኪሞች ፌደሬሽን (FIGO) ሲሆኑ፤ በመድረኩ የጤና ሚኒስቴር ኃላፊዎች፣ ዶክተሮች፣ የሙያ ማኅበራት ተወካዮች እና አጋር አካላት ተሳትፈዋል።
በጤና ሚኒስቴር የእናቶች፣ ሕፃናትና አፍላ ወጣቶች ጤና መሪ ሥራ አስፈፃሚ ሲስተር ዘምዘም መሐመድ እንደገለጹት፣ ከወሊድ በኋላ የሚከሰት የደም መፍሰስ የእናቶች ሞት ዋነኛ ምክንያት ነው። አጠቃላይ ከወሊድ ጋር ተያይዞ ከሚከሰተው የእናቶች ሞት 61 በመቶ የሚሆነው በደም መፍሰስ የሚመጣ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥም 81 በመቶው ከወሊድ በኋላ በሚከሰት የደም መፍሰስ ሳቢያ የሚከሰት ነው።
ለዚህ አደጋ የደም ማነስ፣ ከዚህ ቀደም የደም መፍሰስ ያጋጠማቸው፣ መንትያ ወይም ትልልቅ ፅንስ የያዙ፣ ከአምስት በላይ የወለዱ እና ምጥ የረዘመባቸው እናቶች በከፍተኛ ሁኔታ ተጋላጭ መሆናቸው ተመላክቷል። እንዲሁም ከወሊድ በኋላ የማህፀን አለመኮማተር፣ የማህፀንና የብልት መቀደድ እና የእንግዴ ልጅ በወቅቱ አለመውጣት ዋና ዋናዎቹ መንስኤዎች እንደሆኑ ተገልጿል።
እናቶችን ከዚህ አደጋ ለመታደግ የጋይድላይን እና የሪስፖንስ ፕላን ክለሳዎች መደረጋቸውንና እንደ ትራንዛሚክ አሲድ እና ካርቢቶሲን ያሉ መድኃኒቶችን ተደራሽ የማድረግ እንዲሁም በ15 ደቂቃ ውስጥ የተቀናጀ ሕክምና የመስጠት አሠራር በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ተጀምሮ ወደ ሌሎች የጤና ተቋማት እየተስፋፋ እንደሚገኝ ተነግሯል።

በኢትዮጵያ የጤናና የሥነ-ሕዝብ ዳሰሳ መረጃ መሠረት እ.ኤ.አ በ2000 ዓ.ም የነበረው የእናቶች ሞት በ100 ሺህ በሕይወት ከሚወለዱ ሕፃናት 871 የነበረ ሲሆን፣ አሁን ላይ ወደ 141 ዝቅ ማለቱ ተገልጿል። በ2030 ዓ.ም ደግሞ ይህንን ቁጥር ወደ 70 እና ከዚያ በታች ለማውረድ በተቀመጠው ግብ መሠረት በደም መፍሰስ መከላከል ሥራ ላይ በትኩረት እንደሚሠራ ተመላክቷል።
በመጨረሻም ባለድርሻ አካላት ቅንጅታቸውን እንዲያጠናክሩ ጥሪ የቀረበ ሲሆን፣ እናቶችም በቤት ውስጥ ከመውለድ ተቆጥበው በጤና ተቋማት በመውለድ ሕይወታቸውን እንዲታደጉ ተመክሯል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ