ሚያዚያ 15 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ)መቀሌ በሚገኘው የዓይደር ሪፈራል ሆስፒታል በቅርቡ የጨረር ሕክምና አገልግሎት መስጠት እንደሚጀመር የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ በተለያዩ የጤና ተቋማት የጨረር ሕክምና አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፤ በአሁኑ ወቅት አገልግሎቱ በስድስት የጤና ተቋማት እየተሰጠ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
ሕክምናው አዲስ አበባን ጨምሮ በጅማ፣ አዳማ፣ ሀረማያ እና በሌሎችም አካባቢዎች እየተሰጠ መሆኑን ያመለከቱት ሚኒስትር ዴኤታው፤ በቅርቡም በመቀሌ ዓይደር ሪፈራል ሆስፒታል ለማስጀመር አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
ከዚህም ባሻገር የካንሰር መድኃኒት አቅርቦት ላይ የነበረውን ክፍተት በመረዳት፤ ችግሩን ሙሉ በሙሉ ባይፈታውም ለ32 የሕክምና ተቋማት በመንግሥት ድጎማ እየቀረበ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የጤና አገልግሎቱን ተደራሽ ከማድረግ ጎን ለጎን ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን የመከላከል ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የገለጹት ዶክተር ደረጄ፤ ማኅበረሰቡ አስቀድሞ ምርመራ የማድረግ ልምዱ መሻሻል ማሳየቱን ጠቁመዋል። በዚህም ባለፈው ዓመት ብቻ ከ24 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የደም ግፊት ምርመራ ማድረጋቸውን አስታውቀዋል።
ጤና ሚኒስቴር የጨረር ሕክምና አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማትን ከማስፋፋት ባለፈ፤ ከታካሚዎች ወረፋ ጋር ተያይዞ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት በትኩረት እየሰራ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው አክለው ገልጸዋል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ