መጋቢት 14 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ) የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት ከክልሉ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ጋር በመተባበር በሚያዘጋጀው “ጉሚ በላል” የሃሳብ መድረክ 50ኛው ዙር፤ “በዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የ50 ሲደመር 1 (50+1) ሚና” በሚል ርዕስ ውይይት እየተካሄደ ይገኛል።
መድረኩን በንግግር ያስጀመሩት የክልሉ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ፤ መንግሥት አካታች፣ ፍትሐዊ እና በወንድማማችነት ላይ የተመሠረተ የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታን ለማሳካት በቁርጠኝነት እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል። ይህንን ግብ ዳር ለማድረስም መንግሥት የዲሞክራሲ ሥርዓትን የሚያጸኑ ተቋማትን በመገንባት፤ ለሁሉም የምትመች፣ ሁሉንም በእኩል የምታገለግል እና ሁሉንም የምትመስል ሀገር ለመገንባት አጽንዖት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን አስረድተዋል።
የተጀመረውን የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ከሁሉም ዜጎች ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚጠበቅ ሲሆን፤ በተለይም ሴቶች ዋና ተዋናይ በመሆን መጻኢ ጊዜን የመገንባት ኃላፊነት እንዳለባቸው ኃላፊው አሳስበዋል።
የኦሮሚያ ክልል ሴቶችና ሕፃናት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ መብራት ባጫ በበኩላቸው፤ የሴቶች ተሳትፎ በተረጋገጠባቸው ሀገራት የዲሞክራሲ ሥርዓታቸው በጽኑ መሠረት ላይ የተገነባ መሆኑን ጠቅሰው፣ በተቃራኒው የሴቶች ተሳትፎና መብት ባልተከበረባቸው ሀገራት የዲሞክራሲ ሥርዓቱ ያልዳበረና ኋላቀር መሆኑን ገልጸዋል። በተጨማሪም ያለ ልዩነት የዜጎች ተሳትፎ ሲረጋገጥ፣ ሁሉም ዜጋ የበይ ተመልካች ከመሆን ይልቅ የሥርዓቱ ባለቤት እንደሚሆን አስረድተዋል።
በሀገራችን ሴቶች ቁጥራቸው ከ50 በመቶ በላይ መሆኑን የጠቀሱት ኃላፊዋ፤ መንግሥት በሚኒስትሮች ደረጃ የሴቶችን ቁጥር 50 በመቶ ማድረጉ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ግንባታ መሠረት የጣለ እርምጃ መሆኑን አብራርተዋል። በአሁኑ ወቅት ሴቶች ወደ ኃላፊነት መምጣት ብቻ ሳይሆን፣ በተመደቡበት የሥራ መስክ ተጨባጭ ውጤት በተግባር እያሳዩ መሆኑን በመግለጽ፤ ያለባቸው ድርብ ኃላፊነት ወደ ኋላ ሳይገታቸው የድርሻቸውን እየተወጡ እንደሚገኙና ሴቶች የሀገር ምሰሶ መሆናቸውን አጽንዖት ሰጥተዋል።
የሴቶች ተሳትፎ ባልተረጋገጠበት እውነተኛ ዲሞክራሲ እውን ሊሆን እንደማይችል የገለጹት ወይዘሮ መብራት፤ በመጨረሻም በሀገሪቷ ከ50 በመቶ በላይ ድርሻ ያላቸውን ሴቶች ለማሳተፍ ታቅዶ ይህ መርሃ ግብር መዘጋጀቱ ትልቅ ዕድል መሆኑን ገልጸዋል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ