መስከረም 27 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ) የአፍሪካ አቅም ግንባታ ፋውንዴሽን (Africa Capacity Building Foundation – ACBF) ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ ለ33 ዓመታት በአፍሪካ አገሮች የመልካም አስተዳደርና የኢኮኖሚ ልማት አቅምን በማጎልበት ረገድ ወሳኝ ሚና መጫወቱን አስታውቋል።
ይህ የአፍሪካ ህብረት ልዩ የአቅም ግንባታ ኤጀንሲ ለአህጉሪቱ ዘላቂ ልማት ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል ተብሏል።
ፋውንዴሽኑ በዋነኛነት ከ40 በሚበልጡ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ ባሉ የመንግሥትና የግል ተቋማት እንዲሁም በማህበረሰብ ክፍሎች የአቅም ማጎልበቻ ፕሮግራሞች ላይ ትኩረት አድርጎ ከ700 ሚሊዮን ዶላር በላይ ድጋፍ አድርጓል።
በተጨማሪም ACBF በአፍሪካ ውስጥ ከ34 በላይ የአስተሳሰብ ማዕከላት (Think Tanks) ጋር በትብብር በመስራት፣ መረጃን መሠረት ያደረገ የፖሊሲ አወሳሰን እንዲኖር አስችሏል ነው የተባለው።
በዚህም ከ20 በላይ የአፍሪካ አገሮች የልማት ተግባራት ተጠቃሚ ሆነዋል።
የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ በበኩላቸው ኢትዮጵያም በገንዘብ ሚኒስቴር በኩል አባል መሆኗን ገልጸው፤አፍሪካ የልማት ወጭዋን በተቻለ አቅም መሸፈን እንድትችል ለማድረግ ያለመ ፋውንዴሽን መሆኑን ገልጸዋል።
ፋውንዴሽኑ የ11ኛው የአፍሪካ አስተሳሰብ ማዕከል ጉባኤ (Africa Think Tank Summit) ዋና አስተባባሪ በመሆን ከ8-10 ባለው ጊዜ ውስጥ ከ200 በላይ ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት መድረክ አዘጋጅቷል።
በዚህ ጉባኤ ላይ “በአፍሪካ ኢኮኖሚ ለውጥ ላይ ያለው የሀገር ውስጥ አቅም ግንባታ” በሚል መሪ ቃል፣ በተለይም አህጉሪቱ ለልማት የሚያስፈልጋትን የሀገር ውስጥ የፋይናንስ ምንጮችን የማሰባሰብ ሥራን ጨምሮ በልዩ ልዩ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ውይይት ተደርጓል።
የአፍሪካ አቅም ግንባታ ፋውንዴሽን በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ ውስጥ ከሚገኙ ከ50 በላይ የአስተሳሰብ ማዕከላት ጋር በመስራት የፖሊሲ ምርምርና ትንተና በማካሄድ የአህጉሪቱን ኢኮኖሚ አመራር ለማጠናከር እየሰራ ነው ተብሏል።
ፋውንዴሽኑ በዘርፉ ባለው ሰፊ ልምድ እና ስትራቴጂያዊ ኢንቨስትመንቶች የአፍሪካን የልማት አቅም በማጠናከር ለጠንካራና የራሷን ዕድል ለመወሰን ለቻለች አፍሪካ መሰረት እየጣለ ይገኛል።

የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ 👉 https://t.me/menaharia_fm
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን 📞
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63
(https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
የቀጥታ ስርጭት 🔊 👉 https://zeno.fm/radio/menahria-99-1-3pw1/ (https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
ምላሽ ይስጡ