መስከረም 22 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ) መስከረም 5 ቀን 2018 ዓ/ም ሁሉም ትምህርት ቤቶች የመማር ማስተማር ስራ መጀመራቸው ይታወቃል። ከዚህ ጋር ተያይዞ ተማሪዎች በትምህርት ቤትም ሆነ ከትምህርት ቤት ውጪ ከስነምግባር ውጪ የሆኑ ተግባራት እንዳይፈፅሙ በክፍለ ከተሞች የትምህርት ፅ/ቤት በኩል ከመምህራን ፣ከወላጆች እና ተማሪዎች ጋር የውይይት እና ህገ ደንቦችን የማሳወቅ ስራ መሰራቱ ተገልጿል ።
ተማሪዎች ወደ ተለያዩ ሱስ ውስጥ እንዳይገቡ ለመከላከል ከትምህርት ቤት ውጪ የሚገኙ አዋኪ ቤቶች ላይ ግብር ሃይል ተቋቁሞ በጥናት እየተለየ እርምጃ መወሰዱን ለጣቢያችን የገለፁት የለሚኩራ ክፍለ ከተማ ትምህርት ፅ/ቤት ሃላፊ ለሊስቱ ተስፋዬ ናቸው፡፡
ትምህርት ቤት ውስጥም አንዳንድ ተማሪዎች ለሱስ አጋላጭ የሆኑ ነገሮችን ይዘው የሚገቡበት ሁኔታ በመኖሩ ፍተሻዎች ተጠናክረው እንዲደረጉ ትምህርት ቤቶች እየሰሩበት መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በዋናነት ወላጆች የልጆቻቸውን ሁኔታ የመከታተል ድክመት መኖሩን በመጥቀስ በዚህ ጉዳይ ላይ ትምህርት ከመጀመሩ በፊት ይህንን እንዲያሻሽሉ ከወላጆች ጋር በውይይቱ ላይ መግለፃቸውን አስታውሰዋል፡፡
የቦሌ ክፍለከተማ ትምህርት ፅ/ቤትም በዚህ ጉዳይ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የገለፁት የፅ/ቤቱ ሃላፊ አቶ መስፍን ታደሰ ናቸው፡፡ ከዚህ ቀደም ወደ ሱስ የገቡ ተማሪዎችን ከማባረር ይልቅ በተለያዩ ክበባት ታቅፈው ግንዛቤ እንዲያገኙ ሲደረግ እንደነበረ በመጥቀስ የ2018 የትምህርት ዘመን ላይም በዚህ ጉዳይ ላይ ስልጠና የመስጠት ስራ እንደሚከናወን እና የሱስ ተጠቂ የሆኑ ተማሪዎችን የመለየት ስራ እየተከናወነ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ትምህርት ቤት አካባቢ የሚገኙ አዋኪ ቤቶች ላይ የሚደረገውን ቁጥጥር በዋናነት ከሚሰሩ ግብር ሃይሎች ጋር በቅንጅት የመቆጣጠር ስራ እንደሚያከናውኑም አንስተዋል፡፡ ተማሪዎች ሱስ ውስጥ እንዳይገቡ ከፍተኛ ክትትል በወላጆች እና በህብረተሰቡ በከል ሊደረግ እንደሚገባ ተመላክቷል፡፡
ምላሽ ይስጡ