ከዓመታት በፊት በነበረው የሰሜኑ ጦርነት ተፈናቅለው ወደ ቀድሞ ቀዬአቸው ያልተመለሱ ዜጎች ቁጥር በርካታ መሆኑን እና በዘላቂነት ማቋቋም እንዳልተቻለ ተገልጿል፡፡
ከፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት በኋላ የምግብ ድጋፍ ሲደረግ የቆየ ቢሆንም፣ እስካሁን ከምዕራብ ትግራይ ምንም አይነት ተፈናቃይ መመለስ እንዳልተቻለ የጊዜያዊ አስተዳደሩ አመራር እና የስምረት ፓርቲ ከፍተኛ የሚዲያና ኮምዩኒኬሽን አባል አቶ ጣዕመ አረዶም ለጣቢያችን ገልጸዋል፡፡
በጎረቤት ሃገር ሱዳን ወደ 70 ሺህ የሚሆኑ ተፈናቃዮች አሁንም ድረስ በአሳሳቢ ሁኔታ እንደሚገኙ የገለፁት አቶ ጣዕመ፣ አሁን ላይ ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደርና ከፌደራል መንግስት ጋር በመሆን ወደ ቀዬአቸው ለመመለስ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ከክልል ጀምሮ እስከ ፌደራል መንግስት ድረስ ተፈናቃዮችን ለመመለስ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ ቢሆንም፣ በክልሉ የሚኖሩ ከ600 ሺህ እስከ 1 ሚሊዮን የሚሆኑ ተፈናቃዮች በብርድ፤ በርሃብ እና በሽታ እየተሰቃዩ እንደሚገኙ ገልጸው፣ አስቸኳይ የምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ድጋፎች ያስፈልጋቸዋል ብለዋል።
አሁን ላይ ክልሉ ምንም እንኳን አንጻራዊ ሰላም ያለው ቢሆንም፣ ተፈናቃዮችን መልሶ ለማቋቋም ከመስራት ይልቅ ወቅታዊ አሳሳቢው ነገር በልቶ የማደር ጉዳይ ስለሆነ የእለት ምግብ ማቅረብ ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡
በክልሉ እና ከክልሉ ውጭ ያሉ ተፈናቃዮችን ወደ ቀድሞ ቀዬአቸው ለመመለስ በጋራ መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ