ፍ/ቤቱ በአርባምንጭ ከተማ ባለ 2 እና ባለ 3 እግር ተሽከርካሪዎችን በመስረቅ፣ ተባበሪ በመሆን፣ በመግዛት፣ ወደ ተለያዩ አካባቢዎች ወስደው በመሸጥ፣ በማሻሸጥ እና መሰል የወንጀል ድርጊቶች ላይ በተሰማሩ 7 አካላት ላይ የቅጣት ውሳኔ አስተላልፏል።
ወንጀሉን የፈጸሙት እነዚህ አካላት ከ22 እስከ 40 ዓመት ዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ወንዶች ሲሆኑ 1ኛ እና 2ኛ ተከሳሽ ወጣት ሄኖክ ኃይሉና ወጣት ወርቁ መሰለ በአርባምንጭ ከተማ የጫሞ ቀበሌ፣ 3ኛ ተከሳሽ ወጣት አስናቀ አበበ በዳውሮ ዞን የጋሳ ወረዳ፣ 4ኛ፣ 6ኛ እና 7ኛ ተከሳሾች አቶ ተምራት ቶማስ፣ ወጣት በረከት ቶንቶሼ እና ወጣት በረከት ወጋሶ የቦድቲ ከተማ እንዲሁም 5ኛ ተከሳሽ አቶ ተስፋዬ ኤልያስ የሁምቦ ከተማ ነዋሪዎች መሆናቸውንም የክስ መዝገቡ መረጃ ያሳያል።
ግለሰቦቹ በተለያዩ ጊዜያት በአርባምንጭ ከተማ ከተለያዩ አካባቢዎች ልዩ ልዩ ባለ 2 እና ባለ 3 እግር ተሽከሪካሪዎችን ከቆሙበት መሪ በመስበር፣ በተመሳሳይ ቁልፍ በመክፈት፣ ተከራይቶ በመጥፋት፣ አሽከሪካሪውን በማፍዘዝ እና መሰል የማጭበርበሪያ ስልቶችን በመጠቀም ድርጊቶቹን መፈፀማቸውም ታውቋል።
ግለሰቦቹ በፈጸሙት ተደራራቢ ወንጀል አቃቤ ህግ የሰውና የሰነድ ማስረጃ አደራጅቶ 13 የኢፌዴሪ የወንጀል ህግ አንቀጾች መተላለፋቸውን ጠቅሶ ክስ በመክፈቱ ባለፉት ወራት ሂደት ላይ ቆይቶ ዛሬ የፍርድ ውሳኔ ተሰጥቶበታል።
በተላለፈው ውሳኔም ከባድ የስርቆት ወንጀል በመፈጸሙ 1ኛ ተከሳሽ ወጣት ሄኖክ ኃይሉ 16 ዓመት ከ6 ወራት ጽኑ እስራት ሲቀጣ ቀሪዎቹም እጃቸው ከተያዘበት ጊዜ ጀምሮ በሚታሰብ 1 ዓመት ከ6 ወራት እስከ 5 ዓመት የሚደርስ የቅጣት ውሳኔ ተላልፎባቸዋል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ