መጋቢት 27 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ) በታሪክ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያደረጉ ሴቶች እንዳሉ መረጃዎች ይጠቁሟሉ፡፡ የታሪክ ባለሙያው አቶ በላይ ስጦታው እንደሚሉት ኢትዮጵያ አሁን ያለችበትን ቁመና ለማምጣት በታሪክ ጉልህ ስራ መስራት የቻሉ ሴቶች በርካታ መሆናቸዉንና የማይተካ ሚና እንደነበራቸዉ ያስታዉሳሉ፡፡
በርካታ ሃገራዊ ሃላፊነትን የተወጡ፤ በንግስታትነት ለሃገራቸዉ የማይተካ ሚናን መወጣት የቻሉ፤ ሙያዊ ሃላፊነታቸዉን ያስመሰከሩና በአለም አደባባይ የኢትዮጵያ ስም ያስጠሩ እንስቶች ቢኖሩም በታሪክ ስነዳም ሆኑ በንግርት እነዚህን ሴት የሃገር ባለዉለታዎች የመዘከር የማስታወስ ልማዳችን ዝቅተኛ መሆኑን የታሪክ ባለሙያዉ ገልጸዋል፡፡ በሀገሪቱ የሚጻፉ ጹሁፎች በይበልጥ እይታቸው ፖለቲካዊ ይዘት ላይ ጥገኛ በመሆኑ የታሪክ ባለዉለታዎችን በተለይም የእንስቶችን ታሪክ ሰንዶ ማስቀመጥ ላይ ክፍተት ፈጥሯል ብለዋል፡፡
የታሪክ እና ባህል ተመራማሪ ፕሮፌሰር አህመድ ዛካሪያ ኢትዮጵያ በቀደመው ጊዜ ጠንካራ የሴት ንግስታት ያላት ሀገር ስለመሆኗ ታሪክን በማንሳት ይጠቅሳሉ፡፡ነገር ግን በቀደመው ታሪክ ውስጥ አስተዋጽዖ ያበረከቱ ሴቶች ግለ-ታሪኮቻቸውን በማጥናት እና በመሰነድ ረገድ ገና ብዙ ያልተሰራበት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በታሪክ ውስጥ ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረከቱ እንስቶችን በተመለከተ በአጫጭር መልኩ የተጻፉ መጣጥፎችን እንዳሉ የሚያነሱት ባለሙያዎቹ ማስፋፋት እና ከፍ ባለ የታሪክ ማህደር ላይ ማስቀመጥ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
ምላሽ ይስጡ