የወረዳ እና የክ/ከተማ ቢሮዎች ወጥ በሆነ አሰራር እንዲሰሩ የሚያስገድድ ስታንዳርድ ወይም ደረጃ መውጣቱን የአዲስ አበባ ከተማ የሲቪል ምዝገባና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ ለመናኸሪያ ሬዲዮ አስታውቋል።
አሁን ላይ በከተማው በ119ኙም ወረዳዎች አንድ አይነትና ወጥ አሰራር ለመስራት የታቀደ መሆኑን፤ ስታንዳርዱ በተለይ ከቢሮ አደረጃጃት አንጻር ሰፋ ያለ መስፈርት ማስቀመጡን በአዲስ አበባ ከተማ የሲቪል ምዝገባና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ በምክትል ዋና ዳይሬክተር ማእረግ የኤጀንሲው አማካሪ አቶ ጥጋቡ ሹሜ ተናግረዋል።
በኤጀንሲዉ የአገልግሎት አሰጣጥን ያሻሽላሉ ተብለው ከተያዙት እቅዶች መካከል የቢሮ አደረጃጀትን በወጥነት ማስተካከልና ማዘመን ነው ሲሉ አቶ ጥጋቡ ገልጸዋል። ከዚህ በኋላ የአገልግሎት ሰጪም ሆነ የተገልጋይ መስተናገጃ ወንበሮችና የቢሮ አቀማመጦች በሁሉም ወረዳና ክፍለ ከተማ ዘንድ በወጥነት እንዲሰራ ስታንዳንርድ መዘጋጀቱን አማካሪው ተናግረዋል።
በሁሉም ወረዳዎች ላይ በአመቱ አጋማሽ ላይ አዲስ ስታንዳርድ ተፈጻሚ ማድረግ ከበጀት አንጻር ያልተገባ ወጪ አያስወጣም ወይ ብለን ላነሳንላቸው ጥያቄ አማካሪው ሲመልሱ ፡ ከረጂ አካላትና ከማህበረሰቡ በተሰበሰበ ድጋፍ እንደሚፈጸም አብራርተዋል፡፡
ከ119ኙ ወረዳዎች በ97ቱ ላይ የአዲሱ ስታንዳርድ ትግበራ መጀመሩን የገለጹት የኤጀንሲው አማካሪ ስታንዳርዱ በሁሉም ወረዳዎች ላይ እንዲተገበር የወጣ በመሆኑ በማይተገብሩት ላይ የቅጣት ውሳኔ እንደሚኖርም አስረድተዋል፡፡
ድምጽ አቶ ጥጋቡ ከቢሮ ቀለም እስከ ወንበርና ጠረጴዛ ብሎም አቀማመጥ ፤ ወረዳና ክፍለ ከተማዎች የስማርት ሲቲ ፕሮጀክቱን መምሰል እንዳለባቸው ነው የኤጀንሲው አማካሪ ለጣቢያችን ያስታወቁት።
ምላሽ ይስጡ