የኤሌክትሪክና ታዳሽ ኃይል ተጠቃሚ ተሽከርካሪዎች አገር አቀፍ ረቂቅ ስትራቴጂ ላይ ዘርፉ ከሚመለከታቸው ሚኒስቴር መ/ቤቶች፤ ሚኒስትሮችና የተቋማት አመራሮች ጋር የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስቴር በትላትናው እለት ውይይት በማድረግ ረቂቁን አፅድቋል፡፡
ኢትዮጵያ ከ4 ቢሊዮን ዶላር በላይ በየአመቱ ለነዳጅ እንደምታወጣ የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር ዶክተር አለሙ ስሜ አንስተው፤ኢትዮጵያ ያላትን ታዳሽ ሃይል በመጠቀም ለነዳጅ የሚወጣውን ወጪ ለሌሎች መሰረታዊ አገልግሎቶች ማዋል እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በስፋት ጥቅም ላይ ማዋል ከነዳጅ ጥገኝነት ከመላቀቅና የአየር ብክለትን ከመቀነስ በተጨማሪ ኢንዱስትሪና የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማድረግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክትም ሚኒስትሩ ገልፀዋል፡፡ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በማስፋፋት የሚስተዋሉ የቻርጅ መሙያ ማዕከላት እጥረትና መሠል ተግዳሮቶችን ለመፍታት ሁሉም አካላት በቅንጅት ሃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ተሸርካሪዎችን ከማስገባት ባሻገር በሃገር ውስጥ ማምረት ላይ መስራት እንደሚገባት የተናገሩት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ ናቸው፡፡
የታዳሽ የሃይል ምንጭ ላይ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የሆነ አቅም እንዳላት ሚኒስትሩ አንስተው በኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎች ላይ በአሁኑ ወቅት በሃገር ውስጥ በተወሰነ መገጣጠም የተጀመረ ቢሆንም ወደ ማምረት ማሳደግ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከቻይና ባለሃቶች ጋር ባላት ስምምነት ተሸርካሪዎቹን በሃገር ውስጥ ከማምረት ባሻገር ባትሪዎቹም በኢትዮጵያ እንዲመረቱ ለማድረግ ንግግር መደረጉን ገልፀዋል፡፡
ዘርፉን ለመምራት የተቀናጀ አሰራር እንደሚያስፈልግ ያነሱት ሚንስትሩ ለተቋማቱ የአቅም ግንባታ የሚያስፈልግ በመሆኑ የሃገር ውስጥ ባንኮች እገዛ ማድረግ እንደሚገባቸው ጠቁመዋል፡፡
ምላሽ ይስጡ