የተለያዩ የክልል ፓርቲዎች በግጭት፣ በበጀት እጥረት እና በውስጥ የአደረጃጀት ችግር ምክንያት የምርጫ ዝግጅታቸው ዝቅተኛ መሆኑን ለጣቢያችን ገልጸዋል፡፡
ጠንካራ አደረጃጀት መመስረት እና በርካታ አባላት ማፍራት እንዳልቻሉ የሚገልጹት የሳልሳይ ወያኔ ትግራይ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ብርሃነ ኣጽብሃ፤ በክልሉ የነበረው ጦርነት ፖለቲካውን መስመር እንዳሳተው ገልጸው፤ የጦርነቱ ተጽዕኖ አባላት ለማሰባሰብ ተግዳሮት እንደፈጠረባቸው አስታውቀዋል፡፡
በክልሉ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሲታሰሩ እንደነበር፤ በነጻነትም የፖለቲካ ቅስቀሳ ለማድረግ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ አለመኖሩን፤ አሁን የሰላም ስምምነቱ ባልተተገበረባቸው አካባቢዎች ተንቀሳቅሶ ለመስራት አስቸጋሪ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ፓርቲው አስቻይ የሰላም ሁኔታ ባለባቸው አካባቢዎች ራሱን ለማጠንከር የሚንቀሳቀስ ቢሆንም ከጦርነቱ በኋላ የህወሃት መከፋፈል በተለያዩ አከባቢዎች ለመንቀሰቀስ ተግዳሮት እንደፈጠረ አመላክተዋል፡፡
በመሆኑም ፓርቲው በተጠቀሱት ችግሮች ምክንያት ለቀጣዩ ምርጫ በቂ ዝግጅት እንዳላደረገ አስታውቀዋል፡፡
የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የፖለቲካ ዘርፍ ሃላፊ ዶ/ር መብራቱ አለሙ ፓርቲው በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ ለቀጣይ ምርጫ የሚያደርገው ዝግጅት አጥጋቢ እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡
በክልሉ ያለው የፀጥታ እና የመሰረተ ልማት ተደራሽነት ችግር ፓርቲው በቂ ዝግጅት እንዳያደርግ ተግዳሮት እንደፈጠረበት ገልጸዋል፡፡
በሌላ በኩል የፓርቲው አባላት በገዥው ፓርቲ ኃላፊነት እና ሹመት ሲሰጣቸው ፓርቲያቸውን የመተው ችግር አንዱ ተግዳሮት እንደሆነባቸው ገልጸው፤ በክልሉ ካለው የቤኒን ፓርቲ ጋር በጋራ ተቀናጀቶ ለመወዳደር በሁለቱ ፓርቲዎች መካከል ሰነድ እንደተዘጋጀና ውይይት እየተደረገበት መሆኑን ዶ/ር መብራቱ አስታውቀዋል፡፡
ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ በቂ ዝግጅት እንዳያደርጉ የውስጥ የአደረጃጀት ችግር፤ የሠላም እጦት፣ የበጀት እና ሌሎችም ችግሮች ተግዳሮት እንደፈጠረባቸው ገልጸዋል፡፡
ምላሽ ይስጡ