ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመተባበር በአማራ ክልል ከሕወሀት ጦርነት ጀምሮ እስካሁን ድረስ ያሉ ግጭቶች እና ውጥረቶች በተማሪዎች፣ በሴቶች፣ በሕጻናት እና በሕዝቡ ላይ ያደረሱትን የአዕምሮ እና የሥነ ልቦና ጫና ምን ይመስላል የሚለውን የዳሰሳ ጥናት ማካሄዱ ተመላክቷል፡፡
ዩኒቨርሲቲው ባጠናው ጥናት ግጭቶች እና ሌሎች ችግሮች የክልሉን ሕዝብ ለከፋ ችግር መዳረጉን አስታውቋል፡፡
ከአማራ ክልል ሴቶች ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ የመወያያ ሃሳበ ያቀረቡት አቶ አስናቀ ለውዬ የተለያዩ ችግሮች ሲፈጠሩ ቀዳሚ ተጎጂዎቹ ሴቶች እና ሕጻናት ናቸው ብለዋል። ከኮሮና ቫይረስ ጀምሮ በሴቶች እና ሕጻናት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሲደርስ ቆይቷል ነው ያሉት። ጉዳታቸው አካለዊ እና ሥነ ልቦናዊ መኾኑንም ተናግረዋል።
በተሠራው የዳሰሳ ጥናት የሴቶች እና የሕጻናት ጉዳት ከፍ ያለ መሆኑ የተመላከተ ሲሆን በክልሉ ባለው አሁናዊ ግጭትም ሴቶች እና ሕጻናት የጉዳት ሰለባ ናቸው ተብሏል፡፡
በአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የትምህርት ባለሙያ ለዓለም መኩሪያው ከኮሮና ቫይረስ ጀምሮ ባሉ ተደራራቢ ችግር ምክንያት ትምህርት በከፍተኛ ደረጃ ተጎድቷል ብለዋል። በተደጋጋሚ ችግሮች ምክንያት የትምህርት ተደራሽነት እና ጥራት ፈተና ገጥሞታል ሲሉ መግለጻቸውን አማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ዘግቧል፡፡
ከሰሜኑ ጦርነት ጀምሮ ባሉ ግጭቶች ምክንያት በርካታ ትምህርት ቤቶች ወድመዋል፣ ከሞራል እና ከሕግ ያፈነገጡ ድርጊቶች ተፈጽመውባቸዋል ብለዋል። በትምህርት ቤቶች ላይ የደረሰው ጉዳት ደግሞ ተማሪዎች በሥነ ልቦና እንዲጎዱ አድርጓቸዋል ነው ያሉት። በጦርነት እና በግጭት ብዙ የከፉ ነገሮችን የተመለከቱ ተማሪዎች በሥነ ልቦና ተጎድተዋል ብለዋል። ተማሪዎች ብቻ ሳይኾኑ መምህራንም የሥነ ልቦና ጫና ሰለባዎች ናቸው ሲሉ ገልጸዋል ነው የተባለው፡፡
በግጭት ምክንያት ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት አይሄዱም፣ ቢሄዱም ምን ይደርስብናል የሚል ስጋት አለባቸው፤ ይህ ደግሞ ለሥነ ልቦና ጫና እየዳረጋቸው ነው ብለዋል። ተስፋ ለማድረግ፣ ለመመራመር እና አዲስ ነገር ለመፍጠር ከሥነ ልቦና ጫና መውጣት አለባቸው ነው ያሉት። ተማሪዎችን ከሥነ አዕምሮ ጤና እና ከሥነ ልቦና ጫና ለማላቀቅ በቅንጅት መሥራት ይጠበቃል ብለዋል።
በአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች መከላከል እና መቆጣጠር ኬዝ ስቲም አሥተባባሪ ቢረሳው ታዛየ አማራ ክልል ረጅም ጊዜ የቆዬ ግጭት፣ የወባ ወረርሽኝ፣ የሀገር ውስጥ ብቻ ሳይኾን ከሱዳን የመጡ ተፈናቃዮች ሁሉ ያሉበት እና ሌሎች ተደራራቢ ችግሮች የደረሱበት ክልል ነው ብለዋል። እነዚህ ችግሮች ደግሞ በማኅበረሰቡ ላይ የአዕምሮ ጤና ችግር እና የሥነ ልቦና ጫና ይፈጥራሉ ነው ያሉት።
ዜጎች ለአዕምሮ ጤና ችግር እየተጋለጡ መኾናቸውንም ተናግረዋል። ግጭቱ ከቀጠለ በርካታ ወገኖች ለአዕምሮ ጤና ችግር ይጋለጣሉ ነው ያሉት። ግጭት በተራዘመ ቁጥር ሰዎች የሚወዷቸውን ሰዎች ያጣሉ፣ ከእንቅስቃሴ ይገደባሉ፣ ጫናዎች ይፈጠራሉ ይህ ሲኖር ደግሞ የአዕምሮ ጤና ችግር ይፈጠራል ሲሉ መግለጻቸውን አሚኮ ዘገቧል፡፡
ምላሽ ይስጡ