የንብረት ግብር ማስተባበሪያ ጊዜያዊ ፕሮጀክት ጽ/ቤት አጥንቶ ያቀረበው በአዲስ አበባ አስተዳደር ፋይናንስ ቢሮ አማካኝነት ሚያዝያ 3ቀን 2015 ዓም በተፃፈ ደብዳቤ ለሁሉም የከተማው አስተዳደር መዋቅሮች የተላለፈው የንብረት ግብር መመሪያ ሕግን ባልተከተለ መንገድና የከተማ አስተዳደሩ ባልሰጠው ስልጣን የወጣ መመሪያ በመሆኑ እናት ፓርቲ የአዲስ አበባ ከተማ ሕዝብን በመወከል መመሪያው እንዲሻር ለፍርድ ቤት ክስ መመሥረቱ ይታወሳል።
በፋይናንስ ቢሮ በኩል ወደ ተግባር እንዲለወጥ የተፃፈው የግብር ማሻሻያ ጥናት ሰነድ በፍርድ ቤቱ መመሪያ መሆኑ ስለተረጋገጠ በፌደራል አስተዳደር ስነ-ስርዓት አዋጅ ቁጥር 1182/2013 አንቀፅ 56(2) መሠረት ተፈፃሚነት ሊኖረው አይገባም በማለት መመሪያው እንዲሻር ፍርድ ቤቱ ጥር 9 ቀን 2017 ዓም በዋለዉ ችሎት ውሳኔ ተሰጥቶ እንደነበር የፓርቲው የህግ ክፍል ሰብሳቢ አ/ቶ ዋለልኝ አስፋው ገልፀዋል።
ውሳኔው በተሰጠ የሰዓታት ልዩነት ተጠሪ የከተማ አስተዳደሩ ፋይናንስ ቢሮ በውሳኔው ላይ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ እስከሚል አፈፃፀሙና በጉዳዩ ላይ ሚዲያ መግለጫ እንዳይሰጥ እገዳ ተጥሎበት እንደነበር የህግ ክፍል ሰብሳቢው አስታውቀዋል።
በዛሬው እለት ቢሮው ያቀረበው ይግባኝ ባለመኖሩ የእግድ ትዕዛዙ የጊዜ ገደቡ ያበቃ በመሆኑ ፓርቲው የፍርድ አፈፃፀም ስልጣን ላለው የአፈፃፀም ፍርድ ቤት ፋይል ለመክፈት ዝግጅት እያደረገ መሆኑን እንዲሁም ለሚዲያ መግለጫ እንዳይሰጥ የእግድ ትዕዛዝ ቀነ ገደብ በማብቃቱ ይህንን መግለጫ መስጠታቸዉን ሰብሳቢው አስታውቀዋል።
እናት ፓርቲ በሕጋዊ መንገድ ተመዝግቦ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል እንደሚያደርግ በመግለጽ የወጣው የጣሪያ ግድግዳ/ንብረት ግብር የሕግ አግባብን ተከትሎ እንዲሻር ያስደረገበትን ጉዞ በሰላማዊ መንገድ ክርክሩን እንደሚቀጥል አስታውቋል። እንዲሁም ከዚህ በኋላም ባሉት ከህግ ያፈነገጡ ሂደቶች ላይ መሰል ሰላማዊ እንቅስቃሴዎችን እንደሚያደርግ ፓርቲዉ ገልጻል፡፡
ምላሽ ይስጡ